Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ 10 ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ተጠናክረው ይቀጥላሉ አለ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት፡፡

የኢንስቲትዩቱ የትንበያ መረጃ እንደሚያመላክተው÷ በግንቦት አጋማሽ አካባቢ ለዝናብ መፈጠር አስዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

በመሆኑም በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ስፍራዎች ላይ ለዝናብ መፈጠር አመቺ የሆኑ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች አንጻራዊ ጥንካሬ ይኖራቸዋል፡፡

በተለይም የምድር ወገብን በማቋረጥ ወደ ሀገራችን ከሚገባው ዕርጥበት አዘል የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ የተሻለ የደመናና የዝናብ ሥርጭት ይኖራቸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ምስራቅ፣ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት ያገኛሉ፡፡

በሚቀጥሉት ቀናቶች ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ጨምሮ የደቡብ ምዕራብ እና የምዕራብ የሀገሪቱ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ (ከ1 እስከ 29 ሚ.ሜ) መጠን ያለው ዝናብ የሚያገኙ ይሆናል፡፡

በተጨማሪም አልፎ አልፎ በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ፣ ምስራቅ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በ24 ሠዓት ውስጥ ከ30 ሚ.ሜ በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በተጨማሪም በጥቂት የደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ እና ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል በበልግ ወቅት በመደበኛነት ትኩረት ከሚሹ የአየር ሁኔታ ክስተቶች መካከል ቀን ላይ የሚኖረው የሙቀት መጠንና ሌሊት ላይ ደግሞ የሚታየው ወበቅ አንዱ ነው።

በግንቦት የመጀመሪያው 10 ቀናት ከሚኖረው ከፍተኛ የፀሐይ ሀይል ጋር በተያያዘ በተለይም በጋምቤላ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና በምዕራብ አማራ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ32 እስከ 39 ነጥብ 6 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.