በኦሮሚያ ክልል ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት መፈናቀላቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በኦሮሚያ ክልል ከሐምሌ ወር ጀምሮ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ምክንያት ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በክልሉ የበልግ ዝናብ መጣል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ለጉዳት መደረጋቸውም ተመልክቷል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ገረመው ኦሊቃ እንዳሉት በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አፋጣኝ ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል።
ለተጎጂዎች የምግብ እና የአልባሳት ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ጀልባ ጭምር በመጠቀም ሰዎችን ከውሃ ውስጥ የማውጣት ሥራዎች ተሰርቷል ብለዋል።
በክረምቱ የአዋሽ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
አዋሽ ወንዝ ብቻም በ16 የክልሉ ወረዳዎች ባሉ 56 ቀበሌዎች በሚኖሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ነው የገለጹት።
በክልሉ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ተሰርተዋል።
ጉዳት በደረሰባችው አካባቢዎች ህብረተሰቡ እርስ በርስ እንዲረዳዳና ከመንግስት የእህል ክምችት በማውጣት ለተጎጂዎች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
በጎርፉ የጠፋውን ሰብል ለማካካስም የውሃ ሙላት መቀነስን ተከትሎ አርሶአደሩ ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲያለማ ይደረጋል ፡፡
በብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ መሰረት የክረምቱ ዝናብ እስከ መስከረም የሚዘልቅ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ህብረተሰቡ አሁንም ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በምዕራብ ጉጂ፣ በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ በምዕራብና ምስራቅ ሸዋ፣ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪ ልዩ ዞን እና በባሌ ዞኖች ላይ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የወንዞች ሙላት መቀነስ እየታየ አብዛኞቹ ተጎጂዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከህብረተሰቡ፣ ከባለሀብቶችና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም የመደገፍ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።