Fana: At a Speed of Life!

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከከተማዋ የንግድ ማህበረሰብ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከከተማዋ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይቱ ላይ መጪውን አዲስ ዓመት በአብሮነትና በመረዳዳት ስሜት መቀበል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለዚህም የንግዱ ማህበረሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ በተማሪዎች ምገባ ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ አቅመ ደካማ ነዋሪዎችን በማገዝ፣ በገበታ ለሸገር እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ለነበራቸው ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩልም ከተማ አስተዳደሩ ለ241 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች መመገቢያና ማብሰያ አዳራሽ ግንባታ፣ ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ ስርጭት፣ ለአንድ ተማሪ አንድ ጫማ መርሃ-ግብር ለ600 ሺህ ተማሪ ፣ የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ለ 400 ሺህ ተማሪ እንዲሁም በመንግስት ትምህርት ቤት ለሚማሩ 600 ሺህ ተማሪዎች የደንብ ልብስ ለማዘጋጀት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የከተማው የንግድ ማህበረሰብም እንደተለመደው ሁሉ አሁንም ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም የተጀመሩ ስራዎችን እንዲደግፍ እና ማህበራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ወይዘሮ አዳነች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ሊተገበሩ በተያዙ ዕቅዶች ዙሪያ እና ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ወይዘሮ አዳነች ከንግዱ ማህበረሰብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተያያዘ ዜና የአዲስ ዓመት በዓልን አስመልክቶ የሚከናወን የማህበራዊ ድጋፍና የአብሮነት ንቅናቄ በተለያዩ ዝግጅቶች ከፊታችን ጳጉሜን 1 እስከ ጳጉሜን 5 በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ፡፡

ንቅናቄው በዋነኛነት የተጀመረውን የፍቅርና የአብሮነት ጉዞ ለማጠናከር፣ አዲሱን ዓመት በተስፋ ለመቀበልና እንኳን አደረሳችሁ ለመባባል፣ የከተማ አስተዳደሩ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የነዋሪዎችን ተሳተፎ ለማሳደግ፣ በጎ ፈቃደኝነትንና የመረዳዳትን ባህል ለማሳደግ፣ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ጋር ይበልጥ አብሮ ለመስራት የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠርና የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት ይረዳል ነው የተባለው፡፡

በዚህም ጳጉሜን አንድ የይቅርታ ቀን፣ጳጉሜን ሁለት የአብሮነት ቀን፣ ጳጉሜን ሶስት የአምባሳደርነት ቀን፣ ጳጉሜን አራት የምስጋና ቀን እንዲሁም ጳጉሜን አምስት የብሩህ ተስፋ ብርሃን ቀን ይከበራል ተብሏል፡፡

በእነዚህ ቀናት ላይም በአስተባባሪዎች በየወቅቱ በሚሰጡ መመሪያዎች መሠረት የከተማው ነዋሪዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.