ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ዝግጅት…
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሀገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣትና የመምረጥ መብታቸውን ለመጠቅም ዝግጁ ነን አሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች፡፡
አስተያየታቸውን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሰጡት ነዋሪዎቹ÷ በምርጫው ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግና የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ሳሙኤል እሸቱ ምርጫ ዜጎች የሀገራቸውን መፃኢ እድል የሚወስኑበት ትልቅ መድረክ መሆኑን ጠቅሶ÷ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን ይመራናል ለምንለው ፓርቲ ድምፃችንን ለመስጠት ዝግጁ ነን ብሏል።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት የማርውሃ ደጀኔ በበኩሏ÷ በምርጫው ለሀገር ሰላምና ልማት ይበጃል የምትለውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቷን ተናግራለች፡፡
የከተማዋ ነዋሪ ብርቱካን ፍቃዱ በምርጫው ዕለት የሚሰጥ እያንዳንዱ ድምፅ ለነገዋ ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥል መሆኑን በማንሳት በዕለቱ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ይመራኛል የምትለውን ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጅት ማድረጓን ነው የገለጸችው፡፡
በግዛቸው ግርማዬ