Fana: At a Speed of Life!

የቦረና ሕዝብ የገዳ ሥርዓት እንዳይጠፋ ጠብቆ ያቆየ ማሕበረሰብ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቦረና ሕዝብ ባህሉን፣ ቋንቋውን እንዲሁም የገዳ ሥርዓትን እንዳይጠፋ ለትውልድ ጠብቆ ያቆየ የተከበረ ማሕበረሰብ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፊና ኦሮሚያ የመስኖ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የተገነባውን የጎሞሌ ወረዳ የመስኖ ግድቦችን በጎበኙበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የቦረና ሕዝብ ድርቅ እና ረሃብ ከአካባቢው እንዲሰደድ ሳያደርገው መቆየቱ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት በአካባቢ የተከሰተው ድርቅ ከ3 ሚሊየን በላይ እንሰሳት መግደሉን አስታውሰው÷ በወቅቱ የማሕበረሰቡ ችግር ሆኖ የቆየው የውሃ ጉዳይ ዛሬ መፈታቱን አመልክተዋል፡፡

በዚህም በአካባቢው 18 ፊና የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች መሰራታቸውን በማንሳት በአንዱ ግድብ ብቻ በቀን ከ150 ሺህ በላይ ከብቶች የውሃው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

ግድቡ ለመጠጥ ውሃ ብቻ ሳይሆን ለግብርና ስራም እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡

በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረው ደርቅ ንዴት እና ቁጭት ፈጥሮባቸው እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ አሁን ላይ እንስሳቱ ጠግበው እና ሕዝቡ ተደስቶ በማየታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውም ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን መልካም ጅምሮች ቢኖሩም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን አንስተው÷ በአካባቢው 30 የፊና ፕሮጀክቶች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

መንግሥት የአካባቢውን ማሕበረሰብ ህይወት ለመለወጥ በቀጣይ ሰፋፊ ስራዎች መስራቱን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.