ደስታ ሙሉ የሚሆነው ሌሎችን መርዳት ሲቻል ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዒድ አል ዓድሃ በዓል በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ሐይማኖታዊ ትዕዛዛትን በማከናወን በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል፡፡
በዓሉ ዒድ አል አድሃ ወይም የዕርድ ቀን (በዓረብኛ የሙን ነኽር) ተብሎ እንደሚጠራ የእስልምና መምህራን ይናገራሉ፡፡
በሂጅራ አቆጣጠር የመጨረሻው ወር የሆነው ዙል ሂጃህ በገባ በዘጠነኛው ቀን አረፋ እንደሚውል እና ዒድ ዓል አድሃ ደግሞ በማግስቱ ወይም በ10ኛዋ ቀን እንደሚከበር ያስረዳሉ፡፡
በዕለቱ የሀጅ ተጓዦች በአረፋ ተራራ ወይም ሜዳ ላይ በመሆን ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ አላህን ይማፀናሉ፤ እዝነቱን ይከጅላሉ፡፡
የአረፋ ተራራን መውጣት ለሁጃጆች ልዩ ትርጉም አለው የሚሉት መምህራኑ፤ የሀጅ ተጓዦች የምኅረት፣ ይቅርታና ጸጸት እንዲሁም መስዋዕትነት ማሳያ በሆነው ቀን ተራራውን መውጣት ከአላህ ጋር የመቀራረብ ዕድል ይሰጣል ይላሉ፡፡
ዒድ ዓል ዓድሃ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን በአላህ ትዕዛዝ ለመስዕዋት ሲያዘጋጁ በምትኩ ሙክት በግ መቅረቡን የሚያስታውስ በመሆኑ የመስዋዕት በዓል ተብሎም ይከበራል።
እንዲሁም አረፋ አዳምና ሄዋን ከገነት ወጥተው ለረጅም ዘመናት ተለያይተው ከቆዩ በኋላ በአረፋ ተራራ ላይ መገናኘታቸው የሚዘከርበት በዓል ነው፡፡
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የዒድ ዓል ዓድሃ በዓልን ሲያከብር ሐይማኖታዊ ትዕዛዛትን በመከወን ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በዓሉን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስገንዝቧል።
የዕርድ ሥነ ሥርዓት የሚከናወነው ጠዋት ከሚሰገደው የዒድ ሰላት በኋላ ሲሆን÷ በዚህ ለምግብ ፍጆታ የሚሰናዳው ዕርድ ለሦስት ይከፈላል።
አንዱ ለተቸገሩ ወገኖች፤ ሁለተኛው ወደ ቤት ለጥየቃ የሚመጡ ወዳጅ ዘመዶች የሚስተናገዱበት እንዲሁም ሦስተኛው ለራስ የሚቀመጥ ይሆናል፡፡
ደስታ ሙሉ የሚሆነው የተቸገሩ ወገኖችን መጠየቅ ሲቻል መሆኑን በመገንዘብ÷ በዚህ አግባብ ዒድ ዓል ዓድሃን (አረፋ) ማክበር ይገባል፡፡
በዓሉ የአላህ ትዕዛዛት የሚፈጸምበት እና የደስታ ነው።