በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ የመስጠት ሂደት በስኬት ተጠናቅቋል – ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ የመስጠት ሂደት በስኬት ተጠናቅቋል አለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ በግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ ሲሰጥ የዋለው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ የመስጠት ሂደት በስኬት ተጠናቅቋል ብለዋል።
በድምጽ ምስጫ ሂደት በአዲስ አበባ ከተማ በጣም ረጃጅም ሰልፎች እንደነበሩ አንስተው÷ በዚህም በሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ አማራ፣ ሶማሌ ክልሎች እና በአዲስ አበባ የድምጽ ቆጠራ አለመጠናቀቁን ገልጸዋል።
በዚህም የመራጮች ቁጥር እስካሁን ተጠቃልሎ አለመግባቱን ተናግረዋል።
ቦርዱ የተለያዩ ቅሬታዎች በተለያየ መንገድ ሲያስተናግድ መቆየቱን አንስተው÷ በሕግ ክፍል በኩል በቀጥታ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ የስራ ክፍል አማካይኝነትና በቅድመ ማስጠንቀቂያ 6412 ስልክ ቁጥር የመጡ ጥቆማና ቅሬታዎች እንደነበሩ አመልክተዋል።
በዚህም ቦርዱ ጥቆማውን በመከተል ከስር ከስር አስፈላጊውን የእርምት ርምጃ ሲሰጥ መቆየቱን እንዲሁም የማጣራት፣ የማረጋገጥና ማስረጃ ማጠናቀር በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለያዩ ቦታዎች የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ተደምሮ ያለቁት ለሕዝብ በይፋ መለጠፉን ገልጸው÷ ወደ ምርጫ ክልል የመጡ ውጤቶችን የመደመር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይ ውጤቱን ለማረጋገጥና ይፋ ለማድረግ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት እንዲመጣ ይደረጋልም ነው ያሉት።
ከመጣ በኋላም እያንዳንዱን የምርጫ ክልል በመለየትና በማየት ተወዳዳሪዎች ያገኙትን ድምጽ በዝርዝር በመመልከት ከመራጭ ሕዝብ ብዛት አንጻር ዋጋ ያላቸውንና የሌላቸውን በመለየት ጥንቃቄ በሞላበት የማጣራት ሂደቱን በማጠናቀቅ የማረጋገጡ ስራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የማረጋገጡ ሥራም በተወሰነ የጊዜ ገደብ መከናወን እንዳለበት በመጥቀስ÷ በጊዜ ገደቡ ውስጥ ለማጠናቀቅ ቦርዱ ጥረት እያደረገና እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በአድማሱ አራጋው