ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያበሰረ ነው – የጋራ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያበሰረ ነው አለ የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት።
የምክር ቤቱ ጸሐፊ አቶ ታሪኩ ድንበሩ የአቋም መግለጫውን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት÷ የዘንድሮው ምርጫ ከቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ እጅግ የተሻለ ሂደት የታየበት ነበር።
የምርጫው ሂደትም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሕዝቡ በነጻነት ድምፅ የሰጠበት መሆኑን ገልጸው÷ አሳታፊና ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ ታሪካዊና ሰላማዊ ሂደት መሆኑንም ተናግረዋል።
በድምጽ መስጫው ዕለት መላው የክልሉ ሕዝብ ከማለዳ ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በትዕግስት ተሰልፎ ድምጹን በመስጠት ያሳየው ጽናትና ቁርጠኝነት በእጅጉ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምርጫው በስኬትና በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዜጎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራትና ምርጫ አስፈጻሚዎች ምስጋናውን አቅርቧል።
የጋራ ምክር ቤቱም በጠቅላላው የምርጫ ሂደት ውስጥ በትኩረት በመንቀሳቀስ የራሱን ድርሻ መወጣቱን ጠቅሰው÷ ምርጫው በሰላማዊ፣ በዴሞክራሲያዊ እና ስኬታማ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ በትብብርና በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን መግለጻቸውን ኢዘአ ዘግቧል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ኢትዮጵያዊያን ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውጭ የስልጣን ባለቤት መሆን እንደማይቻል በተግባር ማሳየታቸውን አስረድተዋል።