Fana: At a Speed of Life!

የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የትኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን – ተመራቂ ወታደራዊ መኮንኖች

በአዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀሰሙት ዘመናዊ ወታደራዊ ሙያና ጥበብ በመታገዝ የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብር ለማስከበር የትኛውንም ዓይነት መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን አሉ የሁርሶ ዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ት/ቤት ተመራቂ ወታደራዊ መኮንኖች።

የሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን የ27ኛ ዙር ፅናት ኮርስ ዕጩ መኮንኖች በትናንትናው እለት አስመርቋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ም/መቶ አለቃ ዘካሪያስ አባተ እንዳሉት÷ በትምህርት ቤቱ ያገኙትን ዘመናዊ ሥልጠናና የዳበረ ልምድ በመጠቀም፣ ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ የተጣለባቸውን ማንኛውንም ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው።

በኢትዮጵያ ዳር ድንበር ላይ በመሰማራት የሀገርንና የዜጎችን ጥቅም አስከብረው ማገልገላቸው፣ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት የመፈጸም ትልቅ ልምድ እንዳስገኘላቸው የገለጹት ደግሞ ሌላው ተመራቂ መኮንን ምክትል መቶ አለቃ ታደለ ናኒዮ ናቸው።

በማሰልጠኛ ቆይታቸው የተሰጣቸው ወታደራዊ የተግባርና የንድፈ ሐሳብ ሥልጠና ወደፊት የሚጠብቋቸውን ቀጣይ ተልዕኮዎች በላቀ ብቃትና ጀግንነት ለመወጣት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

ምክትል መቶ አለቃ ማስተዋል በለጠ በበኩላቸው ፥ ሴት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በማናቸውም ፈተና ውስጥ ሆነው በታላቅ ጀግንነትና ብቃት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር እንዲሁም የዜጎችን ደኅንነትና ከፍታ ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ምክትል መቶ አለቃ ሄዋን አማንም ወደ አመራርነት መሻገር ትልቅ ሀገራዊና የሕዝብ ኃላፊነት መሸከም መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ሀገራቸውን ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች ለመጠበቅ እንዲሁም የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ከፍታ በፅናት ለማረጋገጥ የትኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.