የሀገራችንን እድገት እውን ለማድረግ በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ እየተጓዝን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ግንባታው ለሀገር የሚገባውን ፈጣን እድገት እውን ለማድረግ በትክክለኛው አቅጣጫ በቁርጠኝነት እየተጓዝን መሆናችንን በተግባር አሳይቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ እጅግ ዘመናዊና ፈጣን የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም የተገነቡ ቤቶችን የሚያሳይ የግንባታ ሳይት ጎብኝተናል ብለዋል።
በዚህ ሳይት የ3ዲ ህትመት፣ የቅድመ ዝግጅት ቀላል የአረብ ብረት ግንባታና የኮንቴይነር መኖሪያ ቤቶች የላቁ የግንባታ ዘዴዎች በጥምረት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል።
እያንዳንዳቸው ግንባታዎች ትክክለኛውን ቴክኖሎጂ ስንጠቀም ፍጥነትና ጥራት እርስ በእርስ የማይጋጩ መሆናቸውን ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል፡፡
ጥራታቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶችን ከወራትና ከዓመታት ይልቅ በጥቂት ቀናትና ሳምንታት ውስጥ ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል የታየበት ህያው ምስክር መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ አይነቱ የላቀ ፈጠራ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በቀላሉ ሊተገበር፣ ሊደገምና ሊስፋፋ የሚችል መሆኑን ገልጸው፥ የሀገራችንን የቤት ልማት ፕሮግራም አቅጣጫ በከፍተኛ ደረጃ የመቀየር ኃይል እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ቴክኖሎጂን ከሀገራዊ ርዕያችን ጋር አጣምረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተግባር የተገለጡ መሰል ስራዎቻችን ለሀገር የሚገባውን ፈጣን እድገት እውን ለማድረግ በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ በቁርጠኝነት እየተጓዝን መሆናችንን በተግባር የታየበት ነው ብለዋል፡፡