Fana: At a Speed of Life!

ጀፎር ሀገር በቀሉ እውቀት…

ጀፎር አካባቢ ጥበቃ፣ ማህበራዊ ህይወት፣ ደህንነት፣ የመንገድ እና የከተማ ምህንድስና ጥበብን አቀናጅቶ የያዘ ድንቅ ሀገር በቀል እውቀት ነው፡፡

ጀፎር ማለት የጉራጊኛ ቃል ሲሆን፣ አውራ መንገድ ማለት ነው፡፡ በጉራጌ መንደሮች መካከል ያለ ሰፊና ረጅም መንገድ፤ ጠቀሜታው ከቃሉ ትርጉም በላይ የሆነ እውቀት፡፡

ጀፎር ልዩ የምህንድስና ጥበብ ባህሪይ አለው፡፡ የጀፎር የጎኑ ስፋት ከ60-100 ሜትር እንደሚሆን የሚገለጽ ሲሆን፣ ርዝመቱ ግን አውራ መንገድ (ጀፎር) በሚያቋርጥባቸው አቅጣጫዎች ወንዝ፣ ደንና ትልልቅ ሸለቆዎች እስካላጋጠው ድረስ ቅያሱ ይቀጥላል፡፡ የመንገዱ ስፋት የሚለካው በባህሉ መሠረት በተመረጡ አባቶች ወይም የመሬት ልኬት ዳኞች ነው፡፡

ጀፎር ሀገር በቀል አርክቴክቸርንም ይይዛል፡፡ መኖሪያ ቤቶች ከመንገዱ ግራና ቀኝ በተስተካከለ መስመር ይገነባሉ። መንገዶቹ ዝናብ ሲዘንብ ውሃ እንዳይተኛባቸው ተደርገው ከመሃል ወደ ዳርቻው ዝቅ ያሉ ሆነው ይሰራሉ። ይህም የጭቃ መፈጠርንና የአፈር መሸርሸርን ይከላከላል። ጀፎር ሙሉ በሙሉ በአረንጓዴ ሳር የተሸፈነ ነው። ይህም ለአካባቢው ውበት ከመስጠቱ ባለፈ የአፈር መሸርሸርን ይከላከላል፤ አቧራም እንዳይነሳም ያደርጋል።

የዚህ ሀገር በቀል እውቀት ማህበራዊ እና ደህንነት ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ ጀፎር ለመንደሩ ህዝብ እንደ ትልቅ የመሰባሰቢያ ስፍራ ያገለግላል። ሰርግ፣ ለቅሶ፣ በዓላት እና የዕርቅ ስነ-ስርዓቶች የሚከናወኑትም እዚሁ ሰፊ አደባባይ ላይ ነው። ቤቶቹ ፊታቸውን ወደ ጀፎር አቅጣጫ አድርገው ስለሚገነቡ፣ በማንኛውም ሰዓት ወደ መንደሩ የሚገባ እንግዳ ወይም አደጋ በቀላሉ ይታያል። ይህም የመንደሩን ሰላም ለመጠበቅ ይረዳል። በተጨማሪም ህጻናት ያለ ምንም ስጋት በነጻነት የሚጫወቱበት፣ የፈረስ ጉግስና የተለያዩ ባህላዊ ትዕይንቶች የሚካሄዱበት ሲሆን ለከብቶች መውጫና መግቢያ እንዲሁም ለመዋያነትም እንደሚያገለግል ይገለጻል።

ጀፎር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ ከቤቶቹ በስተጀርባ የጉራጌ ህይወት መሰረት የሆነው የእንሰት እርሻ ይገኛል። ሀገር በቀል እውቀቱ ይህንን የኢኮኖሚ ምንጭ ፊት ለፊት ካለው የጋራ መሄጃ በመለየት የተደራጀ የመሬት አጠቃቀም ፍልስፍናን ይጠቀማል፡፡ ያለ ምንም በካይ እና ዘመናዊ ግብዓት የሚሰራ በመሆኑ ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ፋዳ ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ ተፈጥሮን ሳይበክል ለዘመናት የጸና ዘመናዊ ፍልስፍና በመሆኑ የጥበቡን ታላቅነት ያሳያል።

ኑ፤ ሀገር እንገንባ!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.