Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰላም ጥሪዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቱ በፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ውስጥ እንዳትዘፈቅ ሰላምን ማዕከል ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰላም ጥሪዎች ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ የትጥቅ ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ያለሙ መሠረታዊ የመደመር እሳቤዎች ናቸው።

ጥሪዎቹ መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጠውን ትዕግስት የሚያሳዩ፣ ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችሉ እና ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚጋብዙ ናቸው።

እነዚህ የሰላም ጥሪዎች በዋናነት የጦርነትን ውድመት በማስቀረት፣ የሕዝብን ደህንነት በመጠበቅ እና ሁሉንም ያካተተ ሀገራዊ መግባባት በመፍጠር ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ግጭቶችን በውይይት፣ ማንኛውንም የፖለቲካም ሆነ የማኅበራዊ አመለካከቶች ልዩነቶችን በጠመንጃ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ፣ በውይይትና በድርድር መፍትሔ መስጠት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅኑ አቋሞች ናቸው፡፡

የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ፣ የሰው ሕይወት መጥፋትንና የንብረት ውድመትን ለማስቀረት ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካዊ ሂደቱ እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ጥሪዎች ቀርበዋል።

የመደመር ፍልስፍና ሀገራዊ ራዕይ መሠረቱ ማካተት፣ መቻቻል እና አብሮ መስራት ነው። ይህ አካሄድ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ተፎካካሪዎችንና ልዩነት ያላቸውን ወገኖች በማቀፍ ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት የሚያስችል ሰላማዊ መድረክ ይፈጥራል።

የሰላም ጥሪዎች በንግግር ብቻ የተወሰኑ ሳይሆኑ፣ በታሪክ ውስጥ አሻራቸውን ያኖሩ ተጨባጭ እርምጃዎችም ሆነዋል።

ከእነዚህም መካከል የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያን ሰላም ለማስፈን የተደረገ ትልቅ እርምጃ ሲሆን፣ የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

እንዲሁም መንግሥት ለሰላም ሲል ከፍተኛ ትዕግስት በማሳየት፣ በየጊዜው ለሚነሱ አለመግባባቶች በምክክርና በውይይት መፍትሔ ለማፈላለግ የሚያስችሉ በሮችን ክፍት አድርጓል።

በዚህም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ተሐድሶ በመውሰድ ማህበረሰቡን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰላም አማራጭ ለኢትዮጵያ ብቸኛ እና አስተማማኝ መንገድ መሆኑን በተደጋጋሚ አበክረው ይገልጻሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰላም ጥሪዎች የኢትዮጵያን አንድነት፣ የሕዝቦቿን ሰላምና የሀገሪቱን እድገት ለማረጋገጥ የሚረዱ ቁልፍ ስልቶች ናቸው።

ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን መንግሥት ከሚያደርገው ጥሪ ጎን ለጎን የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰላሙ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.