የስንዴ ምርታማነት ለሀገራዊ ማንሰራራትና ሉዓላዊነት
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር የፖለቲካ ሉዓላዊነትና የኢኮኖሚ ነፃነት መሰረታቸው በውጫዊ ርዳታ ሳይሆን በገዛ አቅም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ነው።
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በምግብ እጥረትና በውጭ ርዳታ ጥገኝነት ውስጥ ቆይታለች። አሁን ላይ ይህንን ታሪክ መቀየር የቻለ የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነትን እውን አድርጋለች።
በዚህ ረገድ በዓመት የስንዴ ምርት ምርት ከውጭ ለማምጣት ብቻ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ታወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ አስቀርታለች።
ይህ ብቻ ሳይሆን ከስንዴ ምርት ወጪ ንግድ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማመንጨት የቻለችበትን የስኬት ታሪክ አስመዝግባለች። ይህ በስንዴ ልማት የታየው እመርታ ከምግብ ዋስትና አልፎ የሀገራዊ ማንሰራራትና የሉዓላዊነት ጉልህ መገለጫ ሆኗል።
የስንዴ ልማት እመርታው ምንጭ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአመራር ሰጪነት እና የማስፈጸም ቁርጠኝነት መሆኑ ግልጽ ነው። “መሬት በጋ ከክረምት ጦም ማደር የለበትም” በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው ንቅናቄ፣ ኢትዮጵያ ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣት በመስኖ ልማት ላይ እንድታተኩር አስችሏታል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታየው ተጨባጭ ዕድገት የሀገሪቱን የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዞ አቅጣጫ ቀይሮታል።
የስንዴ ልማቱ ስኬት በጉልበት ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ የግብርና አሠራር የታገዘ ሲሆን የተሻሻሉ ዝርያዎችን መጠቀም፣ የሜካናይዜሽን አሰራርን ማሳደግ እና የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ማስፋፋት የግብርና ምርታማነቱ አመርቂ እንዲሆን አስችሏል።
ድርቅን፣ በሽታን እና ተባይን የሚቋቋሙ ከፍተኛ ምርት ሰጪ የሆኑ የዘር ዝርያዎችን በማፍለቅ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ መቻሉ የምርት መጠኑን በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ አስችሏል።
ትራክተሮች፣ ኮምባይነር አጫጆች እና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ መዋላቸው የሰው ጉልበትን ከመቀነሱም በላይ የድህረ-ምርት ብክነትን በአግባቡ ለመከላከል አስችሏል።
የባለሙያዎች ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ አርሶ አደሩ ሳይንሳዊ የምርት አያያዝን እንዲከተል አድርጓል።
ኢትዮጵያ ከዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት በፊት ስንዴን ከውጭ የምታስገባ ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትናዋ ጥያቄ ውስጥ የነበረባት ሀገር ነበረች። አሁን ግን በስንዴ ሰብል ላይ ብቻ በተመዘገበው ውጤት የምግብ ሉዓላዊነት ጉዳይ ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ደርሷል።
በባለፈው ክረምት 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር፣ በበጋ ደግሞ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር በአጠቃላይ ከ8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በስንዴ ሰብል መሸፈኑ ሀገራዊ የማንሰራራት ጉዞው መቀጠሉን ያሳያል።
ይህ የስንዴ ልማት ስኬት በሀገሪቱ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ዘርፈ ብዙ ሲሆን፤ የውጭ ምንዛሪ አስተዋጽኦ፣ የአርሶ አደሩ የገቢ አቅም መጨመር እና የምርት አቅርቦት መሻሻል በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ይህ ስኬት የስንዴ ምርትን ከውጭ በመግዛት ይወጣ የነበረው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲቀር በማድረግ፣ ሀገሪቱ የንግድ ሚዛኗን እንድታስተካክል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
አርሶ አደሩ ከምግብ ዋስትና ባለፈ፣ ለገበያ በማቅረብ ገቢውን እንዲያሳድግ እና የኑሮ ደረጃውን እንዲያሻሽል ዕድል ፈጥሯል።
የሀገር ውስጥ ምርት መትረፍረፍ ለዳቦ ፋብሪካዎችና ለሌሎች የምግብ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ አቅርቦትን በማረጋጋት፣ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ይህ ትልቅ ድል ለወደፊት የሌሎች ሰብሎች ልማት እንደ ሞዴል የሚያገለግል እና ለሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረት ይጥላል።