ያደረ ቁስልን በምክክር የሚሽረው ጉባኤ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እውነተኛ ምክክር ከሚነገሩ ቃላት ጀርባ ያሉ ስሜቶችን መረዳት መቻልን፣ በጥልቀት መደማመጥን እና የጋራ ጉዳይን መሰረት አድርጎ መነጋገርን ይፈልጋል፡፡
ዜጎች በሀገር ጥቅም ጉዳይ በጋራ መቆም የሚችሉት ሀሳባቸው ዋጋ እንዳለው በማመን በነጻነት በመወያየት ጥያቄዎቻውን ሲያነሱ፣ በሀገራቸው ጉዳይ ሀሳብ ሲያዋጡ እና ከመንግሥት ጋር መተማመን ሲፈጥሩ ነው፡፡
የሃሳብ ግጭቶችን በምክክር ማረቅ ካልተቻለ እና አለመግባባቶች በይደር የሚታለፉ ከሆነ በዜጎች መካከል ልዩነቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ለልጅ ልጅ የሚተላለፉ ቁርሾዎች የትውልድ ዕዳ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
ምክክር ከትናንት የወረስነውን ስህተት የምናርምበት፣ የዛሬ ቁስሎቻችንን የምንፈውስበት እንዲሁም የነገ ልጆቻችንን ከልዩነት ስጋት አውጥተን ሰላማዊት ኢትዮጵያን ማስረከብ የምንችልበት አይነተኛ መሳሪያ ነው፡፡
ሀገር በዜጎች ልብ ውስጥ ያለች፣ በየሄዱበት ሁሉ ይዘዋት የሚዞሯት፣ ትተው የማይተዋት ወጥተው የማትወጣላቸው የማንነታቸው መገለጫ ስትሆን ሀገር የምትሰራው በጋራ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አስተዋፅኦ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ያልተዋሃደ ዜማ ቢረብሽ እንጂ ለመስማት ጥዑም እንዳይደለ ሁሉ ኢትዮጵያ ተነጣጥሎ የሚያዜምላትን ሳይሆን ከእያንዳንዱ የተዋጣ በጋራ የተዋሃደ ስምምነት ያለውን ዜማ ትሻለች፡፡
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በጋራ የዘመሩትን ያክል ስለ ሀገር በተናጠል የዘመሩበት አያሌ ጊዜያትም አሉ፡፡ እነዚህን የተናጠል ጩኸቶች በጋራ የተዋበ ዜማ ለመቀየር የሀገራዊ ምክክሩ በታሪክ አዲስ ክስተት መሆን ችሏል፡፡
አሁን ላይም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጋራ የተዋበ ዜማ ለመፍጥር አጀንዳ ከማሰባሰብ ጀምሮ በርካታ ምዕራፎችን አልፎ እና በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ለመምከር ተቀምጧል።
ይህ ምክክር ያደረ ቁስልን በመፈወስ የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ የሚተልም እና የብልጽግና መሰረት የሚያስቀምጥ ነው።
በቤተልሔም ግርማ