Fana: At a Speed of Life!

የምክክር ጉባዔው ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ የምትጽፍበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የሚያኮሩ ባህሎች፣ የብዝሃ ውበት ባለቤት ብትሆንም ያለፈችባቸው የታሪክ ገጾች በሙሉ ግን በስምምነት የተሞሉ አልነበሩም።
ትውልድ ያሻገሩ በርካታ በጎ እሴቶች እንዳሉ ሁሉ፣ ዛሬም ድረስ ሀገራዊ አንድነትንና ዘላቂ ሰላምን የሚፈትኑ የታሪክ መጋጨቶችና ዘመን ተሻጋሪ ቅሬታዎች ይስተዋላሉ።
አሁን የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ኢትዮጵያ በእነዚህ ውስብስብ የታሪክ መጋጠሚያዎች ውስጥ አልፋ፤ በገዛ እጇ አዲስና ብሩህ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን “ብዕርና ብራና” ያገኘችበት ታሪካዊ እድል ነው።
ኢትዮጵያ እያከናወነች የምትገኘው የምክክር ጉባዔ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የቀረበ ንጹሕ ብራና ነው።
ብራናው ያለፉ ስህተቶች የሚታረሙበት፣ ማሕበራዊ ትስስር የሚሰናዳበት፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያ የምትመሰረትበትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አዲስ ገፅ ነው።
ብዕሩ ደግሞ የጦር መሣሪያ ሳይሆን የሃሳብ የበላይነት የሚዝፍበት፣ ሃሳብን በሃሳብ የመርታት፣ የመደማመጥና የመካካስ ባህል የሚፈጠርበት ይሆናል።
ይህ ብዕር የአርሶ አደሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና መላው ኢትዮጵያውያን በጋራ የጨበጡት ብዕር ነው።
እያንዳንዱ ዜጋ በጉባዔው ላይ የሚያነሳው ጥያቄና የሚያቀርበው የመፍትሔ ሃሳብ በታሪካዊው ብራና ላይ የሚሰፍር የነገዋ ኢትዮጵያ መመሪያ ይሆናል።
ኢትዮጵያ በገዛ ልጆቿ ጥበብና ብስለት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጀምራለች፤ በብራናው ላይም የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን በብዕሯ ትከትባለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት በተካሄደው የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ እንዳሉት÷ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ጉልህ ሚና አለው፡፡
በሚቀጥሉት ሳምንታት 4 ሺህ ተሳታፊዎችን በአንድ ጣሪያ ስር የሚያሰባስበው የምክክር ጉባዔው÷ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን “ብዕርና ብራና” ያገኘችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
‎የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይለ ርምጃ የሚደመደምበትን አዙሪት ሰብረን በንግግርና በውይይት የምንተካበት ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.