Fana: At a Speed of Life!

የግብፅ መሰረተ ቢስ ውንጀላና የኢትዮጵያ እውነታ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ 85 ከመቶ በላይ የሚሆነው የዓባይ ወንዝ ምንጭ ብትሆንም ለዘመናት በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረሙ ስምምነቶችና ሴራዎች ከአብራኳ በወጣው ወንዝ የመጠቀም መብቷ ተነፍጎ ቆይቷል።
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይ ግብፅ ወንዙ ላይ በብቸኝነት ለማዘዝ የሚያደርጉት ጥረት፣ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ለመገደብ የነበራቸው አቋም እና የሄዱበት የክፋት ጥግ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም፡፡
የካይሮ አቋም ኢፍትሃዊነት፤ ተጨባጭ እውነታን በማወቅ ለመረዳት ካለመፈለግ የመነጨ መስመር ያለፈ ራስ ወዳድነት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን የመጠቀም መብት ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ፍትሃዊ ነው ፤ ምንም እንኳን በግብፅና መሰሎች በበጎ ባይታይም፡፡
ግብፅ በቅኝ ግዛት ወቅት የነበሩ እውቅና የሌላቸው ስምምነቶችን በመጎተት ግድቡ በሀሳብ ደረጃ ተጀምሮ እውን እስኪሆን ድረስ በተለያዩ መድረኮችና አጋጣሚዎች ያረጀ፤ ያፈጀ ሙሾዋን ስታወርድ ቆይታለች፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ይህንን ኢ-ፍትሃዊነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያከትም በማድረግ የኢትዮጵያን የልማትና የኃይል ፍላጎት ማሟላት የጀመረ የትውልድ ቁጭት መልስ ያገኘበት የዜጎች የክብር ህያው ሐውልት ነው፡፡
የግብፅና የአጋሮቿ ጩኸት ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንዳቸው ዓባይን ወደ ቤቱ እንዲመለከት ካደረጉት በኋላም አላበቃም፤ የውሃውን ፍሰት እንደ ምክንያት በማንሳት የተለመደ ውንጀላቸውን ቀጥለውበታል፡፡
የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ፍላጎት በማሟላት፣ ለቀጣናው ሀገራት በቅናሽ ዋጋ የኤሌክትሪክ ሃይል በማቅረብ የኢኮኖሚ ትስስርን ከመፍጠር ባለፈ ዓመታዊ የውሀ ፍሰቱን እንዲያስተካክልና ደለል ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ስጋት እንዳይሆን በአርቆ አሳቢነት የተወጠነ፤ ተወጥኖም እውን የሆነ የአፍሪካ ትልቅ ሃብት ነው፡፡
ያም ሆኖ የኢትዮጵያ ማደግ እንቅልፍ የሚነሳቸው ታሪካዊ ጠላቶች ስልታቸውን እየቀያየሩ እንቅፋቶችን ማኖራቸውን አላቆሙም፡፡
እውነታው ግን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለግብፅም ሆነ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ትሩፋት እንጂ ስጋት አይደለም፡፡
በአንጻሩ ግብፅ በውሃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቷ በኩል የኢትዮጵያን የዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብት እንደወንጀል በመቁጠር መሰረተ ቢስ ውንጀላዋን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ ከሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ “ምንም አይነት የውሃ ችግር ወይም ድርቅ እንደሌለና እስከመጪው መስከረም ወር ድረስ የውሃ ፍሰቱ አሁን ካለው እየጨመረ እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡
ይህ የሚያሳየው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተጽእኖ እንደማያሳድርና የግብጽና የተልዕኮዋ አስፈጻሚዎች እሪታ መሰረተ ቢስ መሆኑን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለመበልጸግ የምታደርገው የትኛውም ጉዞ በትብብር የመልማት እሴትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ የሚያመላክትም ነው
በመልካም ፈቃዱ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.