Fana: At a Speed of Life!

ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያግዝ ስምሪት ተደርጓል አለ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጠንካራና የተረጋጋ ሀገረ መንግሥት ለመፍጠር በሚያግዝ መልኩ የተሳካ ስምሪት ተደርጓል አለ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅትም በ2018 በጀት ዓመት መጀመሪያ ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጣናዊ እና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት በመገንዘብና ስጋቶችን አስቀድሞ በመተንተን ወደ ተግባር መገባቱ ተመላክቷል፡፡

በተለይም የ7ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ደኅንነት ማዕከል በማድረግ የተዘጋጀውን የበጀት ዓመቱን ቁልፍ ግብ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በማሳካት የጸና ሀገረ መንግሥት የመገንባት ሒደቱ ላይ ጉልህ ሚና መጫወት መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅሞች መከበርና ማደግ እንዲሁም ለዜጎች ደኅንነት ስጋት በሆኑ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ወቅታዊ መረጃዎችን በተለያዩ መንገዶች በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና በመተንተን ለውሳኔ ሰጪ አካላትና ለኦፕሬሽናል ግዳጆች ማዋል መቻሉ ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም የሽብርና ታጣቂ ቡድኖችን የመረጃ፣ የሎጂስቲክስ እና የሽብር መረብ በመበጣጠስና ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ በማካሄድ እንደ ሀገር ተደቅነው የነበሩ በርካታ ስጋቶችን ማክሸፍ መቻሉን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ያስገኛቸውን ጥቅሞች በሚጻረር መልኩ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችንና የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመከላከል የዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በተከናወኑ የመረጃ ስምሪቶችና ኦፕሬሽኖች በርካታ በሕገ-ወጥ ተግባር የተሰማሩ ሰዎች ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉንም ጠቅሷል፡፡

አገልግሎቱ በውጭ መረጃ ስምሪቱ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች በላቀ ደረጃ የሚያረጋግጡ ስኬቶችን ማስመዝገቡ ነው የተመላከተው፡፡

በዚህ ረገድ በቀጣናው እና በዓለም-አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ የኃይል አሰላለፍ ለውጦችንና ጂኦ-ፖለቲካዊ አዝማሚያዎችን በመረዳትና በመተንተን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነት፣ጥቅምና ክብር የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎች ለመከተል የሚያግዙ ስትራቴጂካል መረጃዎች መሰብሰብና ማሰራጨት መቻሉና ተጨባጭ ለውጥ መገኘቱን ገልጿል፡፡

ከውጭ አቻ ተቋማት ጋር መርህን በጠበቀ መልኩ የተከናወኑ የአጋርነትና ትብብር ሥራዎችም ሽብርተኝነትን፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ሕገ-ወጥ የገንዘብና የጦር-መሣሪያ ዝውውሮችን በመከላከል ከፍተኛ ሚና እንዳበረከቱ አመልክቷል፡፡

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ በደኅንነት ስምሪት ማዕቀፉ፤ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማትን፤ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ስልታዊ መሰረተ-ልማቶችን እና ታላላቅ ሀገራዊ ኹነቶችን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ የመጠበቅ አቅም እንደገነባ ተጠቁሟል፡፡

አስተማማኝ በሆነ መንገድ በቴክኖሎጂ ጭምር ታግዞ የተገነባው ደኅንነትን የማረጋገጥ ሥርዓት ኢትዮጵያ ተመራጭ የኮንፈረስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን እገዛ ማድረጉም ተገልጿል፡፡

የአቪዬሽን ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ የተከናወኑ ሥራዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተማማኝና ተመራጭ እንዲሆን የራሱን አስተዋጽዖ እያደረገ መቀጠሉ በዓመታዊ ግምገማው ተነስቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ ይህን ስኬት በአሠራርና በቴክኖሎጂ ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራትም ስኬታማ እንደነበሩ የተመላከተ ሲሆን÷የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅትና የሌሎችም ምዘና ተቋማትን ኦዲቶችን ያለምንም ጉድለት ማጠናቀቅ መቻሉና የአቪዬሽን ደኅንነት አዋጅ ተሻሽሎ መጽደቁም በአብነት የሚጠቀሱ ስኬቶች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

እንደ ሀገር የሚቃጡ የሥነ-ልቦና ጦርነቶችን ለመመከትና ለማጥቃት በተሰጡት የማስተባበር ሥራዎች ከጠላት ኃይሎች የሚቃጡ ሙከራዎችን ከማክሸፍ ባሻገር፤ ሀገራዊ አንድነትንና ሕብረትን የሚያፀኑ እንዲሁም የኢትዮጵያን ገፅታ የሚገነቡ ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸው ተጠቁሟል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለመረጃ ለደኅንነትና ለሥነ-ልቦና ጦርነት ስምሪት የሚውሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በራስ አቅም በማበልፀግ የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ የተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ ተስፋ የሚሰጡ ናቸው፡፡

በቀጣይ የላቀ አፈጻጸም ያለው ተቋም ለመገንባት የሚከናወኑትን ሥራዎች ለማጠናከር ሪፎርሙን በአዳዲስ ዕይታዎች የሚያበለፅጉ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.