ለኢትዮጵያ የመከላከያ ቴክኖሎጂ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍተው ዘመናዊ ላቦራቶሪ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በመከላከያ ትምህርት፣ ምርምርና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት የላቀ ማዕከላዊ የምርምር ላቦራቶሪ አስመርቋል፡፡
ዛሬ የተመረቀው ይህ ላብራቶሪ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመታጠቅ በምርምርና ጥናት ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኘውን የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑ ተመላክቷል።
ላቦራቶሪው በዋናነት በመከላከያ ትምህርት፣ በሳይንሳዊ ምርምርና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚያሟላ ማዕከል በመሆን የኢትዮጵያን የመከላከያ ባለሙያዎች በዘመናዊ እውቀት፣ በላቀ ክህሎትና በፈጠራ የማብቃት ራዕይን ሰንቋል።
በተጨማሪም የሀገር መከላከያ ዘመናዊነትን ለማፋጠን፣ የሀገር ውስጥ ምርምርና ፈጠራን ለማበረታታት፣ የቴክኖሎጂ ልማትን ለማጎልበትና የሰው ኃይል አቅምን ለማሳደግ ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ያለው ነው።
የላቀ ማዕከላዊ የምርምር ላቦራቶሪ ማዕከሉ በኢትዮጵያ መከላከያ እና በዓለም አቀፍ አጋር ተቋማት በተለይም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ትብብር መገንባቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩንቨርሲቲን የሪፎርምና ራስን የማዘመን ጉዞ የሚያሳየው ይህ የልህቀት ማዕከል በተለይም ሀገርን ከሳይበርና አዳዲስ የደህንነት ስጋቶች ለመጠበቅ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ከ75 በላይ የትምህርት መርሐ ግብሮች እስከ ፒኤችዲ ደረጃ በማስተማር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ግዙፍ ቤተሙከራ እውን ያደረገው ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በፈረንጆቹ ግንቦት 2023 ባደረገው ስምምነት መሰረት ነው።
በ20 ሺህ 850 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈው ላብራቶሪው ዋነኛ ትኩረቱ የቴክኖሎጂ ሀሳቦችን ማመንጨት፣ ቴክኒካዊ ድጋፍ መስጠትና ወደ ትግበራ መቀየር ሲሆን፥ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ሰባት ላብራቶሪዎችን አስተሳስሮ በውስጡ ይዟል።
እነዚህ ዘመናዊ የላብራቶሪ ማዕከላት የሳይበር ደህንነት፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የ ‘3D’ ህትመትና ፕሮቶታይፕ፣ የኮሙኒኬሽን ኢንጂነሪንግ፣ የአውቶሜሽን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የነርሲንግ ላብራቶሪዎች ናቸው።
እነዚህ ዘርፎች በልዩ ትኩረት የተመረጡት ዓለም አቀፍ አዳዲስ የደህንነት ፈተናዎችን በብቃት ለመመከት፣ አዳዲስ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ለመክፈት እንዲሁም ለሌሎች ላብራቶሪዎች እንደ ሞዴል እንዲያገለግሉ በማሰብ ነው።
በተለይም እንደ ሀገር ትልቅ ፈተና የሆነውን የሳይበር ተጋላጭነት ለመመከት ዩኒቨርሲቲው የወሰደው ይህ ተነሳሽነት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ዩኒቨርሲቲው ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እና ከ400 በላይ ምሁራንን ያቀፈ ሲሆን፥ የላብራቶሪው እውን መሆን የኢትዮጵያን የመከላከያ ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል ነው።
በዓለምሰገድ አሳዬ