Fana: At a Speed of Life!

“ብናለማው አያልቅም!” የባሌ ተፈጥሯዊ ገጸ-በረከት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ ማሻገር እንዲሁም ዘርፉን ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ማድረግ የ«መደመር» መንግሥት ዋና የትኩረት አቅጣጫ ነው።

በዚህ ስትራቴጂካዊ ርዕይ መሰረት ለዘመናት በበቂ ሁኔታ ሳይታይ የቆየው የባሌ ዞን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ዛሬ አዲስ ህይወትና ነፍስ ዘርቶ የልማት ማዕከል ለመሆን በቅቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) «ባሌ ሰፊ ሀብት ያለበት እና ብናርሰውና ብናለማበት ቶሎ የሚያልቅ አይደለም» ሲሉ የገለጹት እውነት፣ የስፍራውን ወሰን የለሽ ተፈጥሯዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም በአጭሩ የሚያስረዳ ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ስነ-ምህዳራዊ ገጽታዎችና እልፍ ተፈጥሯዊ ፀጋዎች የተገነባች ናት። ከእነዚህ መካከል በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የባሌ ዞን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቱሪስት መዳረሻነቱ የፊት መስመር ተሰላፊ ነው።

የባሌ ምድር እና በውስጡ የሚገኘው የሶፍ ዑመር ዋሻ የኢትዮጵያን ጥልቅ ማንነት፣ የዘመናት ታሪክና ያልተነካ የተፈጥሮ ውበት የሚመሰክሩ ሕያው ማዕዘናት ናቸው።

ከባህር ጠለል በላይ ከ1,200 እስከ 1,385 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘውና በምስራቅ ባሌ የሚካተተው የሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የዌብ ወንዝ ለዘመናት ዓለቱን እየቦረቦረ የፈጠረው ከመሬት በታች የሚገኝ ድንቅ የኖራ ድንጋይ ዋሻ ነው።

በመሬት ጥናት ባለሙያዎች ግምት ከአምስት ሚሊየን ዓመታት በፊት መፈጠር የጀመረው ይህ ዋሻ፣ በተፈጥሮ የተቀረጹ ግዙፍና ረዣዥም ምሰሶዎችን ያቀፈ ሲሆን በዓለም ላይ ካሉ ረዣዥም የተፈጥሮ ዋሻዎች አንዱ ተደርጎም ይጠቀሳል።

ዋሻው ስያሜውን ያገኘው በቦታው ኖረው ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ያስተምሩ ከነበሩት ከሼክ ሶፍ ዑመር መሆኑ ይነገራል።

የባሌ ዞን ከሶፍ ዑመር በተጨማሪ በዩኔስኮ በዓለም ተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበውን የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ የሀገራችን ሁለተኛው ከፍተኛ ቦታ የሆነውን የቱሉ ዲምቱ ተራራ ጫፍን፣ እና በብዝሃ-ህይወት የበለፀገውን ጥቅጥቅ ያለውን የሃረና ደን በውስጡ የያዘ የውበት ማዕከል ነው።

እነዚህን መሰል ቅርሶች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ስልጣኔና ተፈጥሮ ሀብት መሆናቸውን በመገንዘብ፣ መንግሥት ለአካባቢው መሰረተ ልማት ዝርጋታና ውበት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተንቀሳቅሷል።

የመንገድና የአገልግሎት ተቋማት መሻሻላቸው፣ መዳረሻዎች ዘመናዊ መልክ እንዲይዙ መደረጉ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ፍሰት በከፍተኛ መጠን ጨምሮታል። ይህም የኢትዮጵያን የ10 ዓመት የቱሪዝም ስትራቴጂካዊ ግብ ስኬታማ የሚያደርግ አቅም ፈጥሯል።

በስፍራው የተከናወኑት የልማት ስራዎች የተፈጥሮ ሀብቱን ከመጠበቅ ባሻገር ለአካባቢው ህብረተሰብ ዘላቂ ጥቅም ማምጣት ጀምረዋል።

በተለይም የቱሪዝም አውታሩ መስፋፋት ለባሌ ወጣቶች አዲስ የኢኮኖሚ ተስፋና የስራ እድል የፈጠረ ነው።
በቱሪዝም መዳረሻዎቹ ስራ ላይ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በስፋት እንዲሰማሩና የአካባቢው ማህበረሰብ የቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉም ለዘላቂ ልማት ዋስትና ጥሏል።

የሀገሪቱን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብት ለኢኮኖሚ እድገት ማዋል መቻሉ የኢትዮጵያን አዎንታዊ ገጽታ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ አድርጎታል።

በባሌ ዞንና በሶፍ ዑመር ዋሻ የታየው የልማትና የመሰረተ ልማት ስራ፣ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ የሰጠው ቀዳሚ ትኩረት ውጤት ማምጣቱን የሚያረጋግጥና የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን ህያው ማሳያ ነው።

ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ባሌ ካለው ሀብት ልክ አንጻር አሁንም ሰፊ ስራዎችን መስራት ይገባናል፤ የባሌና መሰል ቅርሶች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ስልጣኔ መሠረቶች መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል ሲሉ ነው አጽንዖት የሰጡት።

በሶስና አለማየሁ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.