“አንድ” ቁጥር ብቻ አይደለም
“የሺህ ማይል ጉዞ በአንዲት ርምጃ ይጀመራል” ይባል የለም?
በሕይወት ዘመናችን የምንመኛቸው ትልልቅ ሕልሞች፣ የምንመኛቸው ስኬቶች እና ልንደርስባቸው የምንመኛቸው ማዕረጎች ሁሉ መነሻቸው ያቺ «አንድ» የምትል ትንሽ ነገር ነች።
ቁጥር «አንድ» በሒሳብ ስሌት ውስጥ ሰንሰለቱን የምትጀምር ቀላል አኃዝ ልትመስል ትችላለች፤ በሕይወት ስሌት ውስጥ ግን የዓላማ መነሻ፣ የፅናት መሠረት እና የምዕራፍ መክፈቻ ቁልፍ ነች።
ሮበርት ኪዮሳኪ (Rich Dad Poor Dad) በተሰኘው መጽሐፉ «ትልቁ ለውጥ የሚመጣው ትናንሽ ርምጃዎችን በውሳኔ መውሰድ ሲጀመር ነው» እንዳለው፣ ሕይወታችንን የሚቀይሩት ግዙፍ ታምራቶች ሳይሆኑ፣ በየቀኑ የምንወስዳቸው ጥቃቅን የቁርጠኝነት ርምጃዎች ናቸው።
ትልቅ ተራራ ለመውጣት የምንጀምረው በተራራው አናት ላይ በመቆም ሳይሆን፣ ከመሬቷ ላይ በሚያርፈው የመጀመሪያው የእግር አሻራችን ነው። ቁጥር አንድ የነገው ታላቅነት የፅንስ ወቅት ነች።
መስከረም አንድ
ለኢትዮጵያውያን መስከረም አንድ የቀን መለወጫ ሰሌዳ ብቻ አይደለም፤ እርሱ የነፍስ ማደሻ፣ የይቅርታ ምድር፣ የሕይወትና የመልካም ተስፋ አዲስ ጅማሮ ታላቅ ምልክት ነው።
መስከረም ሲጠባ ተፈጥሮ አሮጌውን ዝናብና ደመና ጥላ በቢጫ አደይ አበባ እንደምትሸለም ሁሉ፣ የሰው ልጅም ያለፈውን ጭጋግ፣ ሽንፈትና የትናንት ሕመም ከጀርባው ጥሎ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትበት ቅዱስ ወቅት ነው።
በመንገዳችን ላይ የሚገጥሙ ዕንቅፋቶች ራሳቸው አዲስ መንገድ መማሪያዎች ናቸው። መስከረም አንድ ያለፈውን ስህተት እንደ መማሪያ፣ የገጠመንን ፈተና ደግሞ ወደ ተሻለ ስኬት መሸጋገሪያ የድንጋይ ደረጃ አድርገን የምንቀርፅበት የሕይወት ቅኝት ነው።
ያሰብነውን ለመሆን፣ ከፈለግነው ደረጃ ለመድረስ ጉዟችንን ማስተካከል የምንጀምርበትና ሩቅ ላለምነው ግብ የመድረሻ ሀሁ ዛሬ ነው።
እያንዳንዱ ትልቅ ሕልም የራሱ የሆነ የዝግጅት፣ የፅናት እና የትዕግሥት ጊዜ ይፈልጋል። ታላቅ ስኬት የተፈጥሮ ድንቅ ችሎታ ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ የማይወላውል ዓላማና በየቀኑ የሚደረግ ያልተቋረጠ ጥረት ድምር ውጤት ነው።
ዛሬ የምንወስዳት አንዲት ርምጃ የነገው የታሪካችን የመስመር መጀመሪያ ነች። አዲስ ዓመት ሲገባ፣ መስከረም አንድ ሲጠባ፣ የቀን መቁጠሪያው ብቻ ሳይሆን የውስጥ አስተሳሰባችን፣ የታታሪነታችን ወሰን እና የራዕያችን ጥበት መለወጥ አለበት።
ምንም ያህል ሩቅ የሚመስል ተራራ ቢኖር፣ ምንም ያህል ከባድ የሚመስል የሕይወት ግብ ቢጠበቀን፣ መነሻው ዛሬ የምንወስዳት የመጀመሪያዋ ውሳኔ ነች።
መስከረም አንድን የአዲስ ተስፋ፣ የይቅርታ እና የወደፊት ሕልማችን መጀመሪያ በማድረግ የነገውን ስኬታችንን መሠረት ዛሬ በፅናት እንጣል።
መልካም አዲስ ዓመት!
በታሪኩ ለገሰ