በመፍጠን፣ መዝለልና መስፈንጠር የተቃኘው የኢትዮጵያ ዕድገት ጉዞ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የታሪክ ለውጥ በራሱ ፍጥነት ይጓዛል፤ አንዳንዴ በዝግታ እና በተለመደ አካሄድ፣ አንዳንዴ ደግሞ የመንገዱን አቅጣጫ በሚቀይር ፈጣንና ተወዳዳሪ በሆነ መልኩ።
በማንኛውም ሀገር የዕድገት ታሪክ ውስጥ ፈተናዎች ያጋጥማሉ። ልዩነቱ ግን ለእነዚያ ፈተናዎች በሚሰጠው ምላሽ እና በጽናት ደረጃ ይወሰናል።
ፈተናዎች ማምለጫ የሌላቸው እንቅፋቶች ሊሆኑ ይችላሉ፤ አሊያም አዲስ መንገድ ለመቀየስ የሚያስችሉ ድልድዮች።
ኢትዮጵያ የመረጠችው ሁለተኛውን እና የጠበበውን የጽናት መንገድ ነው። ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙንን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጽዕኖዎች እንደ ተስፋ አስቆራጭ መሰናክል ሳይሆን፣ እንደ ታላቅ መነሳሻ በመጠቀም የተሰሩ ሥራዎች ለዚህ ህያው ምስክሮች ናቸው።
ችግሮችን እንደ ውድቀት ከመቁጠር፣ ፈተናውን ወደ አዲስ የሥራ፣ የልማት እና የፈጠራ ዕድል የመቀየር አቅም ሀገራዊ ጥንካሬያችንን እና የሕዝባችንን የመቋቋም ብቃት በተግባር አሳይቷል።
በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች በተደራረቡበት ወቅት ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ፣ ውስጣዊ አቅምን አጥርቶ በማውጣት እና የነበሩትን ማነቆዎች ወደ አዳዲስ የዕድገት በር ከፋች እድልነት በመቀየር ታላቅ ተአምር ተሠርቷል።
ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እያየነው ያለው ለውጥ ተራ የእድገት ጉዞ ወይም ተስፋ የተጣለበት ተራ ጅማሮ ብቻ አይደለም።ይልቁንም በብዙ የዓለም ሀገራት በቀላሉ ሊመዘገብና ሊሳካ የማይችል፣ በመፍጠን፣ በመዝለል እና በመስፈንጠር የሚገለጽ እጅግ ፈጣን እና ታሪካዊ የለውጥና የዕድገት ምዕራፍ ውስጥ ትገኛለች።
ይህ ጉዞ የትናንት ፈተናዎችን የነገ ብሩህ ዕድል አድርጎ የመቅረጽ ጥበብ፣ የጽናት እና የቁርጠኝነት ውጤት ነው።
ይህ የዕድገት ፍጥነት በተለመደው ተራ አካሄድ ለስኬት የሚያደርስ ተራ ርምጃን አይጠይቅም። ከግብርና ማዘመን እስከ ዘመናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ፣ ከግዙፍ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እስከ ታዳሽ ኃይል ማመንጨት እና የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች የተመዘገቡት ውጤቶች ሀገሪቱ በርካታ የልማትና እድገት ምዕራፎችን በፍጥነት በመክፈት ወደ ብልፅግና እየተራመደች መሆኗን ያሳያሉ።
የከተሞች በመሰረተ ልማት መታደስና የኮሪደር ልማት ሥራዎች የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ ከመቀየር ባለፈ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት አዲስ ዕድልን ፈጥረዋል።
የግብርና ምርታማነት በስፋት ማደግ፣ በበጋ ስንዴ ልማት የተመዘገቡት ውጤቶች ሀገሪቱን ከጠባቂነት ወደ አምራችነትና ለጋሽነት ያሸጋገሩ ናቸው።
የሜጋ ፕሮጀክቶች በፍጥነት መጠናቀቅና አዳዲሶች መጀመር የሀገሪቱን ለእድገትና ብልፅግና የመፍጠን ጉዞ አመላካች ናቸው።
እነዚህ ሁሉ ታሪካዊ መሠረቶች የተጣሉት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድና ለቀጣዩ አዲስ ዘመን ነው። አሁን የተመዘገቡት ስኬቶች የጉዞው ማጠቃለያ ሳይሆኑ፣ የኢትዮጵያ ታላቁ አዲስ ዘመን መጀመሪያ ናቸው።
ሀገሪቱ አሁን የያዘችው የዕድገት ፍጥነትና የተገነባው ጠንካራ መሠረት ቀጣዩ ዘመን የብልጽግና፣ የመፅናትና የታላቅነት ዘመን እንደሚሆን በግልጽ ያመላክታል።
ኢትዮጵያ ከትናንት ፈተናዎቿ ይበልጥ የነገ ተስፋዋ የጎላ፣ ከዛሬ ጉዞዋ ይበልጥ የነገው ተስፋዋ የሚያስደንቅ ሀገር ሆና እያበበች ትገኛለች።
ፈተናዎችን ወደ ዕድል የመቀየር ጥበብ፣ በፍጥነት፤ በመዝለልና በመስፈንጠር ያከናወነቻቸው ተግባራት ሁሉ ለቀጣዩ አዲስ ዘመን ትልቅ ብርሃን እና አዲስ ተስፋን ፈንጥቀዋል።
ወደፊታችን ብሩህ የሚሆነው ያለፈውን ታሪክ መሰረት በማድረግ አዲሱን ዘመን በጥበብ፣ በስራ እና በቁርጠኝነት ስንቀበል ነው። አሁን ላይ የደረስንበት የፈጣን ብልጽግና ዘመን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክም ቢሆን የራሷን ሉዓላዊ የዕድገት መስመር መቅረጽ እንደምትችል ማረጋገጫ ነው።
ለኢትዮጵያ አዲሱ ዘመን የምኞት ብቻ ሳይሆን፣ የተግባር እና የላቀ ስኬት ዘመን እንደሚሆን እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችና የተጀመሩ ጥረቶች ማሳያ ናቸው፡፡
በመልካም ፈቃዱ