Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)በቀጣዩ ምዕራፍ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ከንቲባዋ በአዲስ አበባ ምክር ቤት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ሆነው በድጋሚ መሰየማቸውን አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም÷የአዲስ አበባ ህዝብ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት ከተማውን በከንቲባነት እንዲመሩ በድጋሚ ለሰጣቸው እድል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መላው ኢትዮጵያውያን ብሎም የአዲስ አበባ ህዝብ በነቂስ መሳተፉን እና ነዋሪዎቹ ለዲሞክራሲ ግንባታ እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም እና እድገት ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩበት ነበር ብለዋል።

የተለየ የፖለቲካ እሳቤ መኖሩ ጠላትነት አይደለም ያሉት ከንቲባዋ በአዲሱ ምክር ቤት አዳዲስ አባላት እና የተፎካካሪ ፓርቲዎች መካተታቸው ን አንስተዋል።

ከንቲባ አዳነች ሁሉንም የከተማዋን ነዋሪ በእኩልነት እናገለግላለን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በቀጣዩ ምዕራፍ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ የከተማውን ነዋሪ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

ዜጋን በክብር የሚያገለግል ተቋም መገንባት፣ስልጣን የግል ጥቅም ማካበቻ እንዳይሆን ማድረግ፣ፈጣንና ዘመናዊ አሰራርን መዘርጋት እንዲሁም ሙስናን የሚፀየፍ አሰራር እና ማህበረሰብ መገንባት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም አዲስ አበባን የዲጂታል 2030 ዋነኛ ማዕከል እንድትሆን ለማድረግ፣ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር፣ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እንዲሁም የጥቃቅን እና አነስኛ ኢንትርፕራይዞችን ለማጠናከር እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ከተባበርን እንደበፊቱ ካቅድነው በላይ እናሳካለን ያሉት ከንቲባዋ፣ለከተማ አስተዳደሩ ቀጣይ ምዕራፍ የከተማው ነዋሪ የወትሮ ትብብሩን እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.