Fana: At a Speed of Life!

ህንድና ኢትዮጵያ በተለያዩ ወታደራዊ ትብብሮች ዙርያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤንም ሲ)ህንድና ኢትዮጵያ በተለያዩ ወታደራዊ ትብብሮች ዙርያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር እና የህንድ መከላከያ ሚኒስቴር 2ኛውን የመከላከያ የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ጉባዔው የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ትብብር ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማሸጋገር ያለመ ሲሆን ከመከላከያ ልዩ ልዩ ክፍሎች የተውጣጡ ጄነራል መኮንኖች እና ከፍተኛ መኮንኖች ከህንድ ደግሞ የህንድ የመከላከያ ስቴት ሚስተር ሳንጃይ ኩማር በስብሰባው ተገኝተዋል።
የመከላከያ የዓለምአቀፍ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ፥ የሁለትዮሽ ትብብሩ ማዕቀፍ በመተማመንና በመከባበር የጋራ ጥቅምን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
ትብብሩ የአምስተኛ ትውልድ ጦርነት አቅምን የሚያሳድጉ የቴክኖሎጂ እና የስልጠና ድጋፎችን ማድረግ፣ የመከላከያ አካዳሚዎችን ስርዓተ-ትምህርት ማሻሻል፣ እና የኢትዮጵያ አየር ኃይልና የቴክኖሎጂ ተቋማትን ዘመናዊ የማድረግ ስራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም አንስተዋል።
ሁለቱ ሀገራት በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣በትምህርት፣ በመከላከያ ህክምና አገልግሎት ፣ በባህር ሃይል እንዲሁም በሰላም ማስከበር ዘርፎች እና በሌሎች ቁልፍ ተቋማዊ ተግባራቶች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት መካሄዱን ያነሱት ደግሞ የህንድ መከላከያ ሚኒስቴር ስቴት ሚኒስትር እና ጆይንት ሴክሬተሪ ሳንጃይ ኩማር ናቸው፡፡
በህንድ የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ማዕከል እና በኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት መካከል የጋራ ስልጠናዎችን በተግባር ለማስጀመር፣ እንዲሁም በመከላከያ ሆስፒታሎች መካከል የቴክኒክ እና የህክምና ባለሙያዎች ልውውጥ ማድረግንም ስምምነቱ እንዳካተተ ተጠቁሟል፡፡
በሁለቱ ሀገራት ሰራዊት መካከል የመጀመሪያ የሆነ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማካሄድ፣ የልዑካን ቡድን ጉብኝቶችን እና የልምድ ልውውጦችን ለማስፋፋት ብሎም በመከላከያ ኢንዱስትሪ፣ በምርምር እና ልማት ዘርፎች በጋራ ኢንቨስትመንት ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን ከመከላከያ ሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የሁለቱ ሀገራት አጋርነት እ.ኤ.አ. በ1958 የጀመረ ሲሆን የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በዲሴምበር 2025 እ.ኤ.አ. በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ግንኙነቱ ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ ማደጉ ተመላክቷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.