ፋይዳ የአርሶ አደሮችን የግብርና ፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማሳለጥ ወሳኝ ነው – ዮዳሄ አርዓያሥላሴ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲጂታል መሰረተ ልማትና ፋይዳ መታወቂያ የአርሶ አደሮችን የግብርና ፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማሳለጥ ወሳኝ ነው አሉ የፋይዳ ቨርስ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ፡፡
በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ የሚገኘው ሁለተኛው ፋይናንስ ፎረም 2026 ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
የፋይዳ ቨርስ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ በወቅቱ ፤ የዲጂታል መሰረተ ልማትና ፋይዳ መታወቂያ የአርሶ አደሮችን የግብርና ፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማሳለጥ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ደህንነቱ በተጠበቀ የዲጂታል ማንነት ማረጋገጫ /EKYC/፤ የአርሶ አደሮችና የገጠር መሬት መረጃ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮችን በዲጂታል መሰረተ ልማት በማስተሳሰር የፋይናንስና የሌሎች የግብርና ስራዎች ፍላጎታቸውን ተደራሽ ማድጉን የገለጹት አቶ ዮዳሄ ፤ ማንነትን፣ አርሶ አደሮችና መሬትን በማጣመር በገጠር ፈጣን፣ ቀልጣፋና ትክክለኛ መረጃ መሥጠት የሚያስችል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የግብርና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአርሶ አደሮችን የግብርና ፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማጎልበት ባንኮችና ሌሎች የግል የፋይናንስ ተቋማት ተሳትፏቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡