የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖችን ለመግዛት ተስማማ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ 10 ቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከአሜሪካው የአውሮፕላን አምራች ቦይንግ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
አየር መንገዱ አውሮፕላኖቹን ለመግዛት 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚያደርግ ሲሆን የአውሮፕላኖቹ ርክክብ ከ2033 እስከ 2035 ይከወናል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የግዥ ስምምነቱ አየር መንገዱ ተደራሽነቱን ለማስፋት እና ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት የሚደግፍ ነው።
በተጨማሪም ስምምነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ አገልግሎት አቅሙን በማስፋት አየር መንገዱ ያለውን ዓለም አቀፍ የካርጎ መረብ የበለጠ እንደሚያሳድገው አብራርተዋል፡፡
የቦይንግ 777 ፍሬይተር አውሮፕላን ረጅም ርቀት ለመጓዝ እና ከፍተኛ የጭነት መጠን ለማጓጓዝ የተነደፈ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ካርጎ አገልግሎት በአፍሪካ እና በዓለም ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት የሚኖረውን አቅም በይበልጥ እንደሚያጠናክረው አንስተዋል ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት ሥራ ከአየር መንገዱ አጠቃላይ ገቢ ወደ 23 በመቶ የሚጠጋ ድርሻ እንዳለው የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ የአየር መንገዱን የጭነት አገልግሎቱን ማስፋት እቅድ 2040 ስትራቴጂው አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የቦይንግ የሽያጭና ግብይት ምክትል ፕሬዚዳንት ብራድ ማክሙለን በበኩላቸው÷ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለው የቦይንግ አጋርነት 80 ዓመታትን የዘለቀ መሆኑን ጠቁመው ትብብሩ በአውሮፕላን ግዢ ብቻ የተገደበ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የአየር ጭነት ማጓጓዣ ገበያ ያለውን አቅም ከማስፋት ባለፈ ከአፍሪካ ውጭ ካሉ የንግድ ማዕከላት ጋር ያለውን የካርጎ ትስስር ለማጠናከር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ቦይንግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለውን ረጅም ዘመን አጋርነት በቀጣይም ለማጠናከርና የአቪዬሽን ዘርፉን የወደፊት አቅጣጫ በጋራ ለመቅረጽ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በግዛቸው ግርማዬ