ተቋማትን በማጠናከር በክልሉ ፍትህን እና ሰላምን ለማስፈን እንሰራለን – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የፀጥታ እና ፍትህ ተቋማትን በማጠናከር በአማራ ክልል ፍትህ እና ሰላምን ለማስፈን እንሰራለን አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ሰባተኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መሥራች ጉባዔውን እያካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በድጋሚ የተሾሙት አቶ አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በክልሉ ሰላም እና የፖለቲካ መረጋጋት እንዲመጣ የሚሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መንግሥታችን ጠንክሮ ይሰራል ብለዋል፡፡
ክልሉን ለልማት የተመቸ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር በመነጋገር ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን በማሳደግ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ለዚህም ከወገንተኝንት የፀዱ እና ለህዝብ ጥቅም የቆሙ ተቋማት እንዲገነቡ እንሰራለን ነው ያሉት፡፡
የፀጥታ እና የፍትህ ተቋማትን ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ በክልሉ እና በአጎራባች ክልሎች ያለውን አብሮ የማደግ እና የመልማት አቅምን ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ሰላም በምኞት ብቻ አይመጣም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መወጣት ያለብንን ኃላፊነት እንወጣለን ብለዋል።
አሁን የምናረጋግጠው መዋቅራዊ ለውጥ ፈተናዎችን የሚፈታ ነው በማለት ገልጸዋል።
በመጪዎቹ 5 ዓመታት ዘመናዊ የግብርና አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸው፤ የግሉ ዘርፍ በግብርናው ላይ እንዲሳተፍ እና የውጭ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ ታስቧል ተብሏል፡፡
ዘመናዊ የመስኖ ልማትን መሰረት ያደረገ ምርትን የማሳደግ ተግባር ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት እሴት የታከለባቸውን ምርቶች ለማቅረብ እና የገበያ ትስስርን በመፍጠር ክፍተቶችን ለማጥበብ እንሰራለን ብለዋል፡፡
በእመቤት ሲሳይ