በሲዳማ ክልል ግብርናን በቴክኖሎጂ በማገዝ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል – ዶ/ር መሳይ ሀይሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል የግብርና ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማገዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ፡፡
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት በ7ኛው የምርጫ ዘመን የምስረታ ጉባኤው ዶ/ር መሳይ ሀይሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አድርጎ መርጧል፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡
የኑሮ ጫናዎችን ለማሻሻል እንዲሁም የሕዝቡን የችግር አፈታት ልምዶችን በመጠቀም በጸጥታ፣ በከተማ ልማትና አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
የግብርና ዘርፉን በሜካናይዜሽን በማገዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም በሁሉም ዘርፎች በቴክኖሎጂ የተደገፉ አገልግሎቶችን በማቅረብ የተሟላ የዲጂታላይዜሽን ትግበራን እውን ለማድረግ እንደሚሰራም ነው የገለጹት።
መላው የክልሉ ሕዝብ በመናበብና በመተባበር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በጌታቸው ሙለታ