የክልሉ አዲስ አደረጃጀት ልማትን በአንድ ማዕከል ለመምራት ያለመ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል አዲስ አደረጃጀት አገልግሎቶችን በሁሉም ደረጃዎች ማቋቋም፣ ልማትን ከአንድ ማዕከል መምራት እና የልማት ስራዎችን ወደ ታችኛው መዋቅር ማውረድ ዋነኛ ዓላማው ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ።
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ፥ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ክልሉን ሚመጥን አደረጃጀት ለመፍጠር እየሰራ ነው ።
በዚህም አዲስ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ በአዲሱ መንግሥት ምስረታ ጉባዔ ወቅት የክልሉን አዲስ አደረጃጀት ይፋ መደረጉን አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስት ይህንን ጉዞ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአዲስ የቀበሌ አስተዳደር ማሻሻያዎችን በመተግበር እንደጀመረም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት አደረጃጀት፣ ከክልሉ የሚመጣጠን አወቃቀር ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ነው ብለው በእያንዳንዱ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ድረስ በትኩረት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በግብርናው ዘርፍ ለአርሶ አደሮች እና ለአርብቶ አደሮች ይበልጥ ተደራሽ የሚሆን አደረጃጀት እንደሆነም አመልክተዋል።
አቶ ሽመልስ በአንድ ቦታ ተከማችተው የነበሩ ስልጣኖች እና አገልግሎቶች ወደ ታች ወርደው ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በጸሃይ ጉልማ