Fana: At a Speed of Life!

ጋሞ ዞን እርጥብ ሳር ይዘው የሚነድ እሳት ያጠፉ ጥበበኛ የጋሞ አባቶች መኖሪያ ነው – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አቅም፣ እውቀት፣ ልምድና ጉልበትን በመደመር እንዲሁም ወንድማማችነትን በማጠናከር የልማት ሥራዎችን በትጋት እንሰራለን አሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)።

በክልሉ ም/ቤት መስራች ጉባዔ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሰየሙት ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በአርባምንጭ ከተማ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ ጋሞ ዞን ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሕብረተሰቡ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል።

የጋሞ ዞን እርጥብ ሳር ይዘው የሚነድ እሳት ያጠፉ የጋሞ አባቶች መኖሪያ፣ የጥበብ፣ የሰላምና የመቻቻል ምድር ናት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ይህን ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚውል እሴት ጠብቀው ላቆዩ አባቶች ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል የሚታዩ ችግሮችን በመለየት በእቅድ አካቶ ለመስራት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች መሠረታዊ ናቸው ብለዋል፡፡

በአርባምንጭ ከተማ እንዲሁም በጋሞ ዞን የተጀመረውን ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠልና አዳዲሶችን ለመጀመር የምንሰስተው ጊዜ እና ጉልበት የለም ነው ያሉት።

አርባምንጭን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም የኮንፈረንስ እና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

መፍጠር፣ መፍጠንና መዝለልን መርህ በማድረግ ሥራዎች ታቅደው እንደሚሰሩ ጠቅሰው÷ ሕብረተሰቡም ለክልሉ መንግሥት ጊዜ በመስጠት፣ በጋራ ተጋግዞ በመስራት፣ ወንድማማችነትን በማጠናከር የልማቱ አጋር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በቀጣይ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት በተለይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍና የዴሞክራሲ ልምምድን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በቆይታቸው የአርባምንጭ ሁሉገብ ስታዲየም ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ መመልከታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.