Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ሕንድ ግንኙነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተሸጋግሯል – የሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎ከአክሱማይት እና አዱሊስ ስልጣኔ ዘመን ጀምሮ የነበረው የኢትዮጵያ እና ሕንድ የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተሸጋግሯል አሉ የሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራናያም ጃይሻንካር (ዶ/ር)።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የዐድዋ መታሰቢያን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት÷ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት ከጥንታዊቷ አዱሊስ አንስቶ እስከ ጣሊያን ወረራ ጊዜ ድረስ የዘለቀ ጥልቅ ታሪክ ያለው ነው።

ከዚህ ታሪካዊ ትስስር ባሻገር፣ በርካታ የሕንድ መምህራን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ያበረከቱት አስተዋፅዖ እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደ ሕንድ በማቅናት ያገኙት የትምህርት ዕድል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን መሰረት ያፀና መሆኑን አንስተዋል።

አሁን ላይ ይህ ታሪካዊ ትስስር ይበልጥ ጠንክሮ ወደ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማደጉን የጠቆሙት ሚኒስትሩ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከ600 በላይ የሕንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያለሙ እንደሚገኙ እና ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያንም የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን ሕንድ ጠንካራ ድጋፍ ማድረጓን እና በቀጣይም ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ ቴክኖሎጂ ፈጣሪነት ለምታደርገው ሽግግር የሕንድ መንግሥት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በዓለምሰገድ አሳዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.