Fana: At a Speed of Life!

መረጃ ተጠቅመን ኢነርጂ እናመርታለን ከአደጋም ራሳችንን እንከላከላለን -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) መረጃ ተጠቅመን እንበላለን፤ ኢነርጂ እናመርታለን፤ ከአደጋም ራሳችንን እንከላከላለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ተገኝተው የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት፤ ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ የሚኖረውን ቁልፍ ሚና አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ለበርካታ ዘርፎች መሠረት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጤና፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የግብርና፣ የአቪዬሽን እንዲሁም የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራዎች ከሚቲዎሮሎጂ መረጃ ጋር በቀጥታ የተሳሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተለይም በግብርናው ዘርፍ በቂ መረጃ ሳይኖር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥም ሆነ ተስማሚ የማምረቻ ጊዜን መምረጥ ፈታኝ እንደሆነ አንስተዋል።

መረጃ ተጠቅመን እንበላለን፤ ኢነርጂ እናመርታለን እንዲሁም ከአደጋ ራሳችንን እንከላከላለን በማለት የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ለሀገር ሁለገብ እንቅስቃሴ መሠረት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ላለፉት ስምንት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተተከሉት ከ56 ቢሊየን በላይ ችግኞች የሚያስገኙትን ዘላቂ ፋይዳ ለመከታተል በኢንስትትዩቱ የሚገኙ ሳይንሳዊ መረጃዎች ድጋፍ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተቋሙ አሁን ላይ ከሳተላይት መረጃዎች ባለፈ በየቦታው ያዘጋጃቸውን የአየር ንብረት ሁኔታ መረጃ ዳሰሳ የሚያከናውኑ መሣሪያዎችን በመጠቀም መረጃዎችን እያሰባሰበና እየተነተነ ለሚመለከታቸው አካላት ማድረስ የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ ፍላጎት አንፃር ይህ በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ ተቋሙን በሰው ኃይልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎችና ወጣቶች ወደ ተቋሙ በመምጣት የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን እንዲማሩና የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.