ከትናንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ የዲፕሎማሲ ቀን እየተከበረ ይገኛል። የዲፕሎማሲ ቀን መከበር ሀገራት ከጎረቤቶቻቸው እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት ጋር የፈጠሩትን ወዳጅነት እንዲሁም ያላቸውን ቁመና መለስ ብሎ ለማየት እድል ይከፍታል።
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለመመለስ የጋራ ደህንነትንም ለማስጠበቅ የጋራ ተጠቃሚነትና አብሮ የማደግ መርህን መሰረት ያደረገ መንገድን ትከተላለች።
ረዘም ያለ የዲፕሎማሲ ታሪክ ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ከበርካታ ሀገራት ጋር ለዘመናት የቆየ ጠንካራ ወዳጅነት አላት።
አሁን ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሚለውን ስም የያዘው ‘ሊግ ኦፍ ኔሽንስ’ እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት የተተካው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች አባል ከመሆን በዘለለ ቁልፍ የሆኑ ጉዳዮች ላይ የላቀ ሀሳብ በማዋጣት የግንባር ቀደምትነት ሚና አላት፡፡
ኢትዮጵያ ጣሊያን ለ5 ዓመታት ወረራ በፈጸመባት ወቅት በጄኔቭ ተገኝታ የጋራ ደህንነት ጥሪ በማቅረብና የዲፕሎማሲ አካሄድን በመከተል የደረሰባትን ወረራ በቅጡ ማስገንዘብ ችላለች።
የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ጎዳናዎቿን በሀገራትና አፍሪካውያን ስም በመሰየም ወዳጅነቷን አሳይታለች። እንደ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ዊንስተን ቸርቸል፣ ካርል ደጎል የመሳሰሉ የወንድማችችነት መንፈስን የሚያጠነክሩ ዲፕሎማሲዋን የሚገልፁ ስያሜዎችን አድርጋለች፡፡
ኢትዮጵያ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ከመስራት ባሻገር በፓን አፍሪካኒዝም ተሟጋችነቷና አፍሪካዊ መፍትሔ ለአፍሪካዊ ችግሮች በሚለው መርህ ትታወቃለች፡፡ በዚህም በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በተግባር ታሳያለች፡፡
የዓለም ስርዓት እየተቀያየረ ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ለየትኛውም ወገን ያላደሉና ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነትን መሠረት ያደረጉ አጋርነቶችን ታደርጋለች፡፡ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ስትሰራ ግን እኔ ብቻ በሚል ሳይሆን አብሮ የማደግ መርህን በመያዝ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ እንዲሁም የባለብዙ ወገን ስምምነቶችን አካሂዳለች፡፡ የብሪክስ አባል በመሆንም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጮችን አሳድጋለች።
አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ኢትዮጵያ አቋም ይዛ ብዙ ሞግታለች። ይህንን አቋሟን የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ በርካቶች በአሁኑ ወቅት በስፋት እያንጸባረቁት ነው።
በቀጣናው ያለውን ሰላምና መረጋጋት ለማስጠበቅ፣ በተባበሩት መንግሥታት ለሚካሄዱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ እያበረከተች ያለችው አስተዋፅኦ ሌላኛው የዲፕሎማሲ ቁርጠኝነቷ ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን መጠቀምና ሉዓላዊነቷን የማስጠበቅ ዲፕሎማሲያዊ ትግል አድርጋ ተጠቃሚነቷን እያጎለበተች ነው። በዚህ ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በርካታ ፈተናዎችንና ጫናዎችን አልፎ ለውጤት መብቃቱ በአብነት የሚጠቀስ ነው።
ዲፕሎማሲ ፍላጎቶችን በሰላማዊና በትብብር መንፈስ ለማሟላት ሉዓላዊነትና ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚደረግ ብልህነትና ጠንካራ የድርድር አቅም በመሆኑ ኢትዮጵያ በአግባቡ እየተጠቀመችበት ትገኛለች።
በሰጥቶ መቀበል የሚያምነው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጠንካራ ዲፕሎማሲ ባለፉት ዓመታት በርካታ የዓለም መሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ አድርጓል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ዓለም የምትገኝበትን የሀይል ሚዛን ፉክክሮች ከግምት በማስገባት፣ ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቅ መንገድ የሰለጠነና ዘመኑን የዋጀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ማካሄዷ በእጅጉ እየጠቀማት ነው።
በቤተልሔም ግርማ