የመደመር መንግሥት ዘላቂ ብልጽግናን ለማረጋገጥና ለትውልድ ወረት ለማቆየት እየሰራ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ዘላቂ ብልጽግናዋን ያረጋገጠች ሀገር ለመገንባትና ለትውልድ ወረት ለማቆየት እየሰራ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራ ክልል ቤተ መንግሥት ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት ትጋት ለሰላምና ልማት ቅድሚያ የሰጠ ነው፡፡
የመደመር መንግሥት ሕልም ከዛሬ መንግስትነት በተሻገረ ለትውልድ ወረት ማቆየትና ዘላቂ ብልጽግናዋን ያረጋገጠች ሀገርን መገንባት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከወርቅ እስከ ነዳጅ፣ ከግድብ እስከ ሪዞርት፣ ከሰው ኃይል ልማት እስከ ከተማ ልማት ድረስ ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ሥራዎች በትጋት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
የመደመር መንግሥት የጠንካራ የአስተዳደር ተቋማት ግንባታ ርዕይ በአማራ ክልል በተግባር እየተገለጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቤተ መንግሥቱ ግንባታ ለዚህ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሚገነባው የቤተ መንግሥት ሕንጻ የአማራ ሕዝብን የከበረ ባህልና ወግ፣ ታሪክ ለማውሳት እንዲሁም የቀደሙ ቤተመንግሥቶችን በማደስ፣ አዳዲስ ግንባታዎችን በጥራት በመስራት ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የሥራ ከባቢን ማሻሻልና ደረጃቸውን የጠበቁ ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት ርዕይን ማዕከል ያደረገ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የባህር ዳር ከተማን ከጣና ሀይቅ ጋር በማስተሳሰር የከተማዋን አቅም የሚያሳድግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ግንባታው ከክልሉ እሴቶችና መለያ ባህሪያት በመነሳት በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የተነደፈ ሲሆን፤ ዘመናዊነትን ከሀገር በቀል እሳቤ ጋር ያጣመረ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጣና እና ዓባይ በሚታዩበት የጣና ማዕዘን ላይ ለሚገነባው የክልሉ ቤተ መንግሥት በቦታ መረጣና ዲዛይን ለሰጡት ሀሳብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ዘመናዊ ቢሮዎችን፣ የኮንፈረንስ ማዕከልን፣ የእንግዳ ማረፊያን ያካተተ ሲሆን፤ የባህር ዳርን ተፈጥሯዊ ውበት ከዘመናዊ የሥነ ሕንፃ ጥበብ ጋር በማጣመር የከተማዋን የቱሪዝም መስህብነትና የኢኮኖሚ አቅም ያሳድጋል ነው ያሉት፡፡
የግንባታው መጀመር ድምጹን ለሰጠን ሕዝብ የተግባር ምላሽ ማሳያ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት ተቋማትን ማዘመን ለተሻለ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በለይኩን ዓለም