መደመር ከዓባይ ጫፍ እስከ አቪዬሽን ከተማ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8 ፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታሪክ ሁልጊዜም በነጋሪዎች ብቻ አይጻፍም፤ አንዳንዴ በግዙፍ ማሽነሪዎች፣ በኮንክሪት ፅናት እና በሕዝብ የጋራ ላብ ጭምር ይተረካል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የአህጉሪቱን የንግድ፣ የኃይል እና የትራንስፖርት ካርታ የመቀየር አቅም ያላቸውን ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ፍጥነት በመገንባት ላይ ትገኛለች፤ ገንብታለችም።
በመደመር መንግሥት የሚተገበሩት እነዚህ ስልታዊ ኢንቨስትመንቶች ሀገራዊ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ፣ የምስራቅ አፍሪካን የጂኦ-ፖለቲካ እና የንግድ ትስስር በአዲስ መልክ እየቀረጹት ይገኛሉ።
ከነዚህ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከልም የኢትዮጵያን የአየር ላይ የበላይነት በአዲስ ምዕራፍ ለመጻፍ የሚያስችለው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተጠቃሽ ነው።
የአሁኑ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሀገሪቱን ፈጣን የንግድና የቱሪዝም ፍሰት መሸከም እስከሚያቅተው ድረስ መጨናነቁ፣ አዲሱን የቢሾፍቱ ሜጋ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲወለድ አድርጎታል።
ይህ በዓመት 100 ሚሊየን መንገደኞችን ለማስተናገድ የተነደፈው ግዙፍ ፕሮጀክት፣ ተራ ማረፊያ ሳይሆን የራሱ ሆቴሎች፣ የጥገና ማዕከላትና የንግድ ቀጠናዎች ያሉት ሙሉ የአቪዬሽን ከተማ ነው። ይህ ግንባታ ኢትዮጵያን የአህጉሪቱ የትራንስፖርትና የኢኮኖሚ ማዕከል ያደርጋታል።
ሌላው የኢትዮጵያውያን የቁጭት፣ የህብረት እና የእንችላለን መፈክር ህያው ምስክር የሆነው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ በኩራት ቆሟል።
ይህ በአፍሪካ ግዙፉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪና የብርሃን ጥማትን በዘላቂነት ከመቅረፉ ባለፈ፣ ለጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ ታዳሽ ኃይል እያመረተ ይገኛል።
ግድቡ የሀገር ውስጥ ድል ብቻ ሳይሆን ምስራቅ አፍሪካን በኃይልና በኢኮኖሚ ያስተሳሰረ ታሪካዊ ድልድይ ነው።
በመደመር መንግሥት ለዘመናት ስንዴን ከውጭ ሀገር በማስገባት የሚታወቀው የሃገራችን የታሪክ ምዕራፍ አብቅቶለታል።
በበጋ ስንዴ የመስኖ ልማት የተመዘገበው ተአምር የኢትዮጵያን የግብርና አቅም ዳግም አስመስክሯል። ዛሬ ሀገራችን የራሷን ፍጆታ በራሷ ምርት ሙሉ በሙሉ መተካት ብቻ ሳይሆን፣ የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ አዲስ የኢኮኖሚ ምንጭ መፍጠር ችላለች።
ለበርካታ ዓመታት ሳይጠናቀቅ ተጓቶ የነበረው የመገጭ ግድብና የመስኖ ፕሮጀክት፣ አሁን ላይ እውን የሆነ የልማት ምልክት ሆኗል።
ቃልን በተግባር የሚተረጉመው የመደመር መንግሥት፣ ይህንን ፕሮጀክት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከፍተኛ ክትትልና ርብርብ ለትንሳኤው እንዲበቃ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት ቀጥተኛ ትዕዛዝ፣ የአቅም ችግር የነበረበት የቀድሞው ኮንትራክተር በአዲስ በመተካቱ ፕሮጀክቱ ዳግም ወደ ስኬት ጎዳና ተመልሷል።
በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገለት ከፍተኛ ክትትል የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 94 በመቶ መድረሱ ተገልጿል፡፡
የግድቡ ሥራ በአሁኑ ወቅት ጥራቱን ጠብቆ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ሲሆን፤ በቀጣይ ጥቂት ወራት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በአጠቃላይ እነዚህ የትራንስፖርት፣ የኃይል፣ የግብርና እና የውሃ ሀብት ሜጋ ፕሮጀክቶች በተቀናጀና በዘመናዊ እውቀት ተሳስረው የነገዋን ታላቅ ሀገር እየቀረጹ ነው።
የመደመር መንግሥት ቃልን በተግባር ለመተርጎም የጀመረው ይህ ያላሰለሰ ጥረት እና የተሳካ ርብርብ፣ ኢትዮጵያ ወደ ላቀ ብልጽግና እንድትሸጋገር ጽኑ መሠረት እየጣለላት ይገኛል።
በሶስና አለማየሁ