መከላከያ ሠራዊት፤ የሕዝብ አለኝታና የማይበገር የሰላም ዘብ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ሉዓላዊነትና ደኅንነት የሚረጋገጠው በጠንካራ ተቋማት፣ በተደራጀ የመከላከያ አቅም፣ በሕዝብ ድጋፍና በወታደራዊ ዝግጁነት ነው።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ዘብ የሆነው መከላከያ ሠራዊትም የሕዝብ አለኝታ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ፣ በወታደራዊ ዲሲፕሊን የታነጸና ለማንኛውም ፈተና ዝግጁ መሆን የሚያስችሉ አቅሞችን ፈጥሯል።
ይህም የሠራዊቱን የውጊያ አቅም ብቻ ሳይሆን ለሀገራዊና ቀጣናዊ ሰላም የሚኖረውን አስተዋጽኦ የሚወስን መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
የመከላከያ ሠራዊት ጥንካሬ የሚለካው በትጥቅና በወታደራዊ ብቃት ብቻ አይደለም፤ ከሕዝቡ ጋር ባለው ትስስር፣ በሚያገኘው ድጋፍና በሚያሳየው የሀገር ፍቅርም ጭምር እንጂ።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በወታደራዊ ሥልጠናና በትጥቅ ዘመናዊነት ብቻ ሳይገደብ፣ ሕዝባዊ ተቀባይነትን፣ የተቋማዊ ኃላፊነትንና የሙያ ሥነ ምግባርን ማካበት ችሏል።
ይህ ትስስር ሠራዊቱ በሚያጋጥሙት ውስብስብ ፈተናዎች ወቅት በቁርጠኝነት እንዲሠራና የሕዝቡን ደኅንነት እንዲያስቀድም የሚያግዘው ዋነኛ መሠረት ነው።
የዘመናዊ ወታደራዊ ኃይል ብቃት ከሰው ኃይል ብዛት በላይ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በመረጃ ልውውጥ፣ በዕቅድ አዘገጃጀት፣ በአመራር ቅልጥፍናና በተቀናጀ የውጊያ አፈጻጸም ይገለጻል።
በመደመር መንግሥት ስኬታማ ሪፎርም ያደረገው የመከላከያ ሠራዊትም የቴክኖሎጂ ዘመናዊነት በወታደራዊ መረጃ ማሰባሰብና መተንተን፣ በሎጂስቲክስ አያያዝ፣ በኮሙኒኬሽን፣ በአየር መከላከያና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተቀናጀ አፈጻጸም እያስመዘገበ ይገኛል።
በወታደራዊ ዲሲፕሊን የታነጸው ሠራዊቱ የትዕዛዝ ሰንሰለትን ማክበር፣ በሕግና በደንብ መመራት፣ የተሰጠውን ተልዕኮ በኃላፊነት መወጣትና በተግባር ቅንጅት ማሳየቱ ተልዕኮውን በስኬት እንዲያከናውን አስችሎታል።
የመከላከያ ሠራዊት ዝግጁነት በችግር ጊዜ ብቻ የሚገነባ አይደለም፤ በቀጣይነት በሚካሄድ ሥልጠና፣ በየጊዜው በሚደረግ የአቅም ግምገማ፣ በትጥቅና በመሣሪያዎች ጥገና፣ በሎጂስቲክስ ዝግጅትና በተግባራዊ ልምምዶች የሚገነባ ዘላቂ አቅም ነው።
መከላከያ ሠራዊቱ ማንኛውም ሁኔታ ሲያጋጥም በተገቢው መንገድ ምላሽ መስጠት የሚችል የሰው ኃይል፣ የትጥቅ አቅም፣ የመረጃ ሥርዓትና የአመራር ቅንጅት በአንድነት አጠናክሯል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደሚሉት÷ የሠራዊቱ ግንባታ ሒደት በትጥቅና ቴክኖሎጂ መዘመን ብቻ ሳይሆን በሰው ኃይል ብቃት፣ በዲሲፕሊን፣ በተግባራዊ ዝግጅትና በተልዕኮ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ነው።
በተመሳሳይ ጊዜ የሠራዊቱ የትእዛዝ ሰንሰለት ጠንካራ ሆኖ መቆየት፣ በሙያዊ ብቃት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መስጠትና የሕግ የበላይነትን ማክበርም እኩል ትኩረት ተደርጎበታል።
መከላከያ ሠራዊት በትንሽ ኪሳራ ድል ማድረግ፣ የሰው ሕይወትን መጠበቅ፣ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መስጠት፣ አላስፈላጊ ጉዳትን መቀነስና የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ከመወጣት አንጻር እያሳየ የሚገኘው እመርታ አበረታች ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሚና በሀገር ውስጥ ደኅንነትና ሉዓላዊነት ጥበቃ ባለፈ በተገቢው የሕግና የሥልጣን ማዕቀፍ ውስጥ በሚከናወኑ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች፣ በቀጣናዊ ትብብርና በጋራ ደኅንነት ጥረቶች ውስጥም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ጀግናው መከላከያ ሠራዊት በትጥቅ የዘመነ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ በዲሲፕሊን የታነጸ፣ በተግባር ዝግጁ የሆነና የሕዝብን እምነት ያተረፈ ሆኖ እንዲቀጥል የተጀመረውን ሥራ ማጠናከር ይገባል።