የመንግሥት የሰላም አማራጭና የህገወጡ ህወሓት ቡድን ተቃራኒ መንገድ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት ለህዝቡ ሰላምና ደህንነት፣ ለሀገሪቱ አብሮነትና ህገ መንግሥታዊ ስርዓት መከበር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በሙሉ ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት በመቀበል ወደ ትግበራ መግባቱ ይታወሳል።
የስምምነቱ መሠረታዊ ዓላማዎችም በሁለቱም ወገኖች በኩል ተኩስ ማቆም፣ በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ፈጥኖ መመለስ፣ ታጣቂዎችን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ አስፈትቶ ወደ መደበኛ ህይወት እንዲቀላቀሉ ማድረግ ነው፡፡
በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለስ እንዲሁም ለሀገሪቱ ህገ መንግሥታዊ ስርዓት ሙሉ እውቅና መስጠት የሚሉ ነበሩ።
መንግሥት በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶች እንዲጠገኑ ባንክ፣ መብራት፣ ቴሌኮምና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲመለሱ እንዲሁም የተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት ያለመታከት ሲፈጽም ቆይቷል።
ይህ የመንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ የመስጠት አካሄድ የህዝቡን ችግርና እንግልት ለመቅረፍ የተሄደ ረጅም ጉዞና ትልቅ የኃላፊነት ርምጃ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በእኛ በኩል መደረግ ያለበትን ሁሉ አድርገናል፤ ህገወጡ ህወሓት ግን ትጥቅ ከመፍታት ይልቅ ወደ መሳሪያ ግዢና ልመና ገብተዋል በማለት የመንግሥትን የሰላም ጉዞና የህገ-ወጥ ቡድኑን የጥፋት ጉዞ ገልጸውታል፡፡
መንግሥት ለሰላም በሩን ክፍት በማድረግ ኃላፊነቱን በሚወጣበት ሁኔታ፣ በተቃራኒው ህገወጡ የህወሓት ቡድን የገባውን ቃል ኪዳን ወደ ጎን በመተው ለሀገራዊ ሰላም ስጋት የሆኑ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል።
ቡድኑ በስምምነቱ መሠረት ታጣቂዎቹን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ሰላማዊ ህይወት ከመመለስ ይልቅ አሁንም የጦር መሳሪያ ግዢና ልመና ላይ መሰማራትን እንደ አማራጭ ወስዶ ነበር።
ወጣቶችን ወደ ሀገር ግንባታ እና ወደ መደበኛ ህይወት ከመመለስ ይልቅ በተደጋጋሚ ወጣቶችን በማፈስ ወደ ውትድርና የመመልመል አደገኛ አካሄድ ላይ መሰማራቱ የቡድኑ ሰላምና መረጋጋትን ጠልነት ማሳያ ነው።
ይህ አካሄድ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ከመጣሱም በላይ በክልሉ አላስፈላጊ ውጥረት እንዲነግስና የህዝቡ የሰላምና የልማት ፍላጎት እንዲስተጓጎል የሚያደርግ ነው።
የሰላም ስምምነት ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ሁለቱም ወገኖች የገቡትን ቃል በታማኝነት ሲተገብሩ ብቻ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም የቆመ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ቢሆንም የህወሓት ተደጋጋሚ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችና የስምምነቱን መርሆዎች የመጣስ ጉዞ ግን የሰላም ሂደቱን ወደኋላ የመለሰና ህዝቡን ለተጨማሪ እንግልት የዳረገ ርምጃ ሆኗል፡፡
መንግሥት ይህንን እኩይ አካሄድ በመረዳት ህግ የማስከበር ርምጃን በመውሰድ፤ የትግራይ ህዝብ ከዚህ ህዝብ ጠል ቡድን ቀንበር እንዲላቀቅ በማድረግ፤ የናፈቀው ሰላም ተመልሶለት፤ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቹ የልማትና የብልጽግና ጉዞውን አሀዱ ብሎ በመጀመር ላይ ይገኛል፡፡
በመልካም ፈቃዱ