የሀገሪቱን እምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም መዋቅራዊ ስብራቶች ሊቃኑ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገሪቱን እምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም አስተሳሰባዊና መዋቅራዊ ስብራቶች ሊቃኑ ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት የመገጭ ግድብ ፕሮጀክትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በርካታ ሀብትና እምቅ አቅም እያላት ወደ ተጨባጭ ውጤት የመቀየር ልምምዷ ውስን ነው፡፡
ድርጁ አቅም ባልተገነባበት ሁኔታ ምንም እንኳን እምቅ አቅም ቢኖርም የዜጎችን ህይወት መለወጥ አስቸጋሪ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ለዚህም የአካባቢው ውሃ እምቅ አቅም ሲሆን፤ ውሃው እያለ የጎንደር ህዝብ ይጠማ እንደነበረና አርሶ አደሩም ማትረፍ ሲገባው ማረስ ሳይችል መቆየቱን ጠቅሰው፤ የተገነባው ግድብ ያን እምቅ አቅም ወደ ድርጁ አቅም የለወጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የልማት ስራዎችን በተፈለገው መጠን እንዳታከናውን ከያዟት ምክንያቶች መካከል የሉዓላዊ አቅም እጥረት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገሪቱ በራሷ ሀብት፣ ተቋማትና ባለሙያዎች የልማት ስራዎችን ጀምራ ለማጠናቀቅ የሚያስችላትን አቅም መገንባት እንዳለባትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ሥራዎችን ከመጀመር በፊት በአስተሳሰብ ደረጃ በበቂ ሁኔታ አለመጨረስና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ተከታትሎ ለውጤት አለማብቃት ሌላው ስብራት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሥራዎች ከዕቅድና ዲዛይን ጀምሮ በበቂ ዝግጅት እንዲከናወኑና እስከ መጨረሻ ድረስ በተከታታይ እንዲመሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የልማት ስራዎችን በተናጠል ማከናወን በቂ እንዳልሆነ በመግለጽ፤ በጋራ ማቀድና ተናብቦ መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
ጎንደር ከመንግሥት መጠየቅ እንዳለበትና መንግሥትም ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
የጎንደር የልማት ጉዞ ጅማሮ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት የሚፈጠረው እርካታ በቂ እንዳልሆነና ብዙ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡
ለዘመናት የተሸከሙትን ድህነትና ችግር በትናንሽ ስኬቶች ብቻ መርካት ጉዳት እንዳለው በማስገንዘብ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በቤተልሔም ግርማ