በሀረሪ ክልል የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር በወላጆች ዘንድ እፎይታ ፈጥሯል – ቢሮው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀረሪ ክልል የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር መተግበር በተማሪዎች እና በወላጆች ዘንድ ትልቅ እፎይታ ፈጥሯል አለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ።
በክልሉ የ2019 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር በተያዘው ወር ውስጥ ይጀመራል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የት/ቤቶች ደረጃ ማሻሻል ዳይሬክተር አቶ መሳይ እሸቱ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፤ በክልሉ እየተተገበረ ያለው የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር ሽፋን አድጓል።
ከቅድመ መደበኛ እስከ 4ኛ ክፍል ባሉ በ68 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው፤ በጀቱ በመንግሥት የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል።
በህብረተሰብ ተሳትፎ በድንበር የለሽ የሀረር ልጆች ማህበር ድጋፍ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያለ አንድ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተያዘው የትምህርት ዘመን በክልሉ መንግሥት በተመደበ 46 ሚሊየን 750 ሺህ 672 ብር በጀት፤ 40 ሺህ 672 ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ መርሐ ግብሩን ለማስጀመር በትምህርት ቤቶች ላይ የቦታና የቁሳቁስ ማሟላት ዝግጅቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የመርሐ ግብሩ መተግበር የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ማሳደጉን፤ መጠነ ማቋረጥን መቀነስ ማስቻሉን አንስተው፤ በተማሪዎች እና በወላጆች ዘንድ ትልቅ እፎይታን መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡
ይህ መርሐ ግብር ለ605 መጋቢ እናቶች፣ ግብአት አቅራቢዎች፣ ትራንስፖርት አገልግሎት እና የጭነት አገልግሎት ለሚሰጡ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን አቶ መሳይ ገልጸዋል፡፡
የመጋቢ እናቶች ጤና ምርመራ እና የንግድ ፍቃድ እድሳት የመሳሰሉ ጥቂት ቀሪ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው አንስተው፤ በዚህ ወር ውስጥ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የምገባ መርሐ ግብሩ እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡
በመልካም ፈቃዱ