የመደመር እይታ የወለደው አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር ፍልስፍና ዋና ዋና ግቦች ከሆኑት መካከል የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ግልጽ ማድረግ ይጠቀሳል።
የመደመር መንግሥት ለዜጎች ምቹ፣ ፈጣን እና ከእንግልት የጸዳ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በርካታ መዋቅራዊ እና ቴክኖሎጂ ተኮር ማሻሻያዎች አድርጓል።
በማሻሻዎቹ የመጣው ውጤት የመንግሥትን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ከተከናወኑት ጥረቶች መካከል የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትልቅ ድርሻ አለው።
የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎች በዲጂታል ክፍያ አማራጮች ማለትም እንደ ቴሌብር፣ ሲቢኢ ብር እና ኦንላይን የባንክ ሥርዓቶች በኩል እንዲፈጸሙ በመደረጉ ጊዜና ወጪን በእጅጉ ቀንሷል።
አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ማጠቃለልና አሰራርን ማቃለል በዋናነት የተከናወነ ሌላኛው ስራ ነው፡፡
ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር የገባው የባለብዙ አገልግሎት ማዕከል የዜጎችን እንግልት በመቀነስ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የመሶብ አገልግሎት ማዕከላት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ሲጓተተቱ የነበሩ ጉዳዮች ባጠረ ጊዜ እልባት እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሯል።
የንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ ማደስ እና የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሂደቶች በኦንላይን ስርዓት እንዲከናወኑ በመደረጉ ኢንቨስተሮች እና ነጋዴዎች ባሉበት ሆነው ፈቃድ የሚያገኙበት አሰራር ተዘርግቷል።
በርካታ የፍትህ እና የሲቪል ምዝገባ አገልግሎቶች በዲጂታል ኔትወርክ ተገናኝተው በተለያዩ ማዕከላት ወይም በዲጂታል መንገድ እንዲደርሱ ተደርጓል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዛሬው ዕለት የደብረ ብርሃን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልገሎትን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ማዕከሉ በከተማዋ ፈጣን እና ዘመናዊ አገልግሎት ወደ ስራ መግባት ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች ለምትገኘው የደብረ ብርሃን ከተማ ትልቅ ዕድል ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በመደመር እይታ ስር የጀመረችው የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ዘመናዊ፣ ቴክኖሎጂ መር እና ዜጋን ማዕከል ያደረገ የመንግሥት አስተዳደር ለመገንባት አስተማማኝ መሰረት ጥሏል።
አሰራሮች ይበልጥ በተያዘው የመሻሻል ጎዳና ተጠናክረው ሲቀጥሉ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በማረጋገጥ በሁለንተናዊ ዘርፍ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ጊዜው ቅርብ ይሆናል፡፡