በመቐለ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስጀመር የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች ተጀምረዋል አሉ የመሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አለማየሁ።
አቶ ዮናስ አለማየሁ እንዳሉት÷ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሀገር በቀል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ሥር በማሰባሰብ ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርግ ነው።
በዲጂታል አገልግሎት ሽግግር አቅጣጫ መሠረት በመላ ሀገሪቱ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች ቁጥር 114 መድረሱንና በዚህም ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውንም ጠቁመዋል።
በመቐለ ከተማም አገልግሎቱ በአፋጣኝ እንዲጀመር ይሠራል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ማዕከሉ ለሕብረተሰቡ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው የመንግሥት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የመቐለ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሺሻይ አማረ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የመንግሥት ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ፣ በማደራጀትና በማዘመን ብልሹ አሠራርን ለመቀነስ እንዲሁም የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ ማዕከሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ለሕዝብ ለማድረስ፣ የነዋሪዎችን የጊዜና የወጪ ብክነት ለመቀነስ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።
የመቐለ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሺሻይ አማረ (ዶ/ር) አቶ ስምዖን ተስፋማርያምን ከጥቅምት 17 ቀን ጀምሮ የከተማዋ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ኃላፊ አድርገው መሾማቸው ይታወሳል።
በግዛቸው ግርማዬ