በዘመናዊ ትጥቅ፣ በሕዝባዊነትና በሥነ-ምግባር የተገነባ ሠራዊት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት ታሪክ ከኢትዮጵያ የነፃነት ታሪክ ጋር በጥልቅ የተሳሰረ ነው።
በተለያዩ ዘመናት ሀገርን ከውጭ ወረራ ለመጠበቅ፣ የሕዝብን ክብርና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተከፈሉ መስዋዕትነቶች በታሪክ ማህደር ውስጥ የማይረሱ ምዕራፎች ሆነው ተመዝግበዋል።
ጊዜዎች ሲቀያየሩ፣ የታሪክ ውጣ ውረዶች ሲፈራረቁ፣ ኢትዮጵያ ግን ሁልጊዜም በጽናት ቆማለች።
የዚህች ታላቅ ሀገር ጽናትና ገናናነት ደግሞ የሠራዊቱ የዘመናት የቁርጠኝነትና የጀግንነት ገድል ድምር ውጤት ነው፡፡
ሠራዊቱ የጦር መሣሪያና የወታደራዊ ኃይል ስብስብ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ሉዓላዊነት ጠባቂ፣ የሕዝብ ደህንነት ጋሻና የሰላም መሠረት ነው።
ከሕዝብ ተለይቶ የሚኖር አካል ሳይሆን፣ ከሕዝቡ የሚወጣ፣ ለሕዝቡ የሚቆምና የሕዝቡን ደህንነት የሚያስቀድም ተቋም የሆነው ሠራዊቱ፤ ከሕዝቡ በመተባበርና በጋራ ኃላፊነት መንፈስን ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኙነት አለው።
ይህም የሀገር መከላከያ ተልዕኮ ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው አስችሏል።
የሰው ኃይሉ የሙያ ብቃት፣ የሥልጠና ጥራት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የተቋማዊ ዲሲፕሊንና የሥነ-ምግባር ደረጃ የሠራዊቱ መገለጫዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዘመናዊ ትጥቅና ቴክኖሎጂን ከሰው ኃይል ልማትና ከሙያዊ ብቃት ጋር በማጣመር የመከላከያ አቅሙን ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት ዘመኑን የሚመጥን አስተማማኝ ቁመና እንዲላበስ አድርጎታል፡፡
ዘመኑ የቴክኖሎጂና የፍጥነት በመሆኑ፣ ሰራዊቱም ከዘመኑ ጋር እኩል እየተራመደ ነው። የዚህ ዘመናዊነት አንዱ ገጽታ የአየር ኃይሉ ነው።
ዛሬ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሰማይ ላይ አይነኬነቱን በዘመናዊ ጄቶች፣ በላቁ ድሮኖች እና በጠንካራ የአየር መከላከያ ስርአቶች አስመስክሯል።
የአየር ኃይል የወታደራዊ መከላከያ አቅምን ከፍ ከሚያደርጉ ወሳኝ የሰራዊት ክፍሎች አንዱ ሲሆን፣ በምድርም ሆነ በሰማይ ሀገሩን ለመጠበቅ የሚያስችልም ሉዓላዊ አቅም ፈጥሯል።
በዘመናዊ ትጥቅ የተሟላው እና በዕውቀት የጎለበተው ይህ ሠራዊት፤ የኢትዮጵያን ጥንካሬ ማሳያ ግልጽ አቅም ነው።
የታጠቃቸው ቴክኖሎጂዎች የሀገርን የአየር ክልል ለመጠበቅ፣ የመረጃ አቅምን ለማጠናከርና ለተለያዩ የመከላከያ ተግባራት የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለማቅረብ ወሳኝ ናቸው።
ታዲያ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመናዊነት የሚታየውም በትጥቁ ብቻ ሳይሆን፣ በሙያተኞቹ እውቀት፣ በሥልጠናቸውና ቴክኖሎጂውን በኃላፊነት በመጠቀም ብቃታቸው ጭምር ነው።
ከዘመናዊ ትጥቅና ከቴክኖሎጂ በላይ ሰራዊቱን በልዩ ሁኔታ የሚገልጸው የሥነ-ምግባር ግንባታው ነው።
ሙያዊ ዲሲፕሊን፣ ለሕግ የበላይነት ተገዢነት፣ ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ ለሲቪል ሕዝብ ደህንነት ቅድሚያ መስጠትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ማክበር የዚህ ሠራዊት መለያዎች ናቸው።
የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና የመረጋጋት ጉዳይ ከአንድ ሀገር ወሰን በላይ የሚዘልቅ በመሆኑ፣ በሰላም አስከባሪነት፣ በደህንነት ትብብርና በቀጣናዊ መረጋጋት ላይ የሚደረጉ ጥረቶች ሠራዊቱ በግንባር ቀደምትነት በመምራት እውቅናን አትርፏል፡፡
ለኢትዮጵያውያን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ማለት መጠሪያ ስም ብቻ አይደለም፤ የመስዋዕትነት፣ የታሪክ፣ የኃላፊነትና የሀገር አንድነት ምልክት ነው።
በመልካም ፈቃዱ