Fana: At a Speed of Life!

የከተሞች ልማት ዕይታ በተግባር የተገለጠባት አዲስ አበባ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል ከመሆኗ ባሻገር የፈጠራ፣ የባህል፣ የንግድና የዘመናዊ የከተማ ሕይወት ማዕከል ለመሆን ያላትን አቅም ማሳደግ እየቻለች ነው።
ይህንን በዘላቂነት ለማሳካትም የልማት ስራዎቿን ከከተማ ፕላን፣ ከባህልና ቱሪዝም፣ ከወጣቶች የሥራ ዕድል፣ ከዲጂታል አገልግሎቶችና ከዘላቂ ልማት ጋር በማቀናጀት ውጤታማ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች።
አዲስ አበባ ተወዳዳሪ የሆኑ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲኖሯት የተፈጥሮ ፀጋዎቿን በአግባቡ በመጠቀም በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች እና በሌሎችም የከተማ መልሶ ግንባታ እንቅስቃሴዎች በጉልህ ተንጸባርቋል፡፡
የተፈጥሮ ውበት ከዘመናዊ የስነ-ህንፃ ጥበብ ጋር በማዋሀድ የተገነቡት ወዳጅነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ እና ሌሎች የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገር የሚመጡ ጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ላይ ይገኛሉ።
አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጎብኚዎቿ ተመራጭ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ጉልህ ሚና ማበርከት ጀምረዋል፡፡
በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በከተማ ውበትና በአረንጓዴ ልማት የሚከናወኑት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎች የተሻለ የኑሮና የአገልግሎት አማራጭ ለመፍጠር ያግዛሉ።
በተለይም የከተማዋን ወንዞች ከብክለት በማጽዳት፣ የተፈጥሮ ሚዛናቸውን በማስመለስና የወንዝ ዳርቻዎችን ለሕዝብ ምቹ ወደሆኑ ስፍራዎች በመቀየር የአካባቢ ጥበቃንና የነዋሪዎችን ጥቅም ማጣጣም እየተቻለ ነው።
በየአካባቢው የለሙ የኮሪደር ልማቶች፣ ለወጣቶች የተገነቡ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የህጻናት መጫዎቻዎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ መሰረተ ልማቶች እና ሌሎችም ፕሮጀክቶች የአዲስ አበባን የስዕበት ማዕከልነት ከፍ አድርገዋል፡፡
አዲስ አበባ የመደመር መንግሥት የከተሞች ልማት ዕይታ በተግባር የሚገለጽባት ከተማ ከመሆኗም በላይ ለሌሎች ከተሞች ሊጋራ የሚችል ተሞክሮ እያፈራች ነው።
የዚህ ተሞክሮ ዋና ትርጉም የከተማ ልማት ሰውን፣ አካባቢንና ኢኮኖሚን በአንድነት ሲያስብ ዘላቂና ውጤታማ እንደሚሆን ማሳየቱ ነው።
አዲስ አበባ የዛሬውን ልማት የነገ ብልጽግና መሠረት በማድረግ፣ ለነዋሪዎቿ የተሻለ ኑሮ የሚፈጥርና ለቀጣይ ትውልድ የሚበጅ ከተማን በጋራ የመገንባት ጉዞዋን ቀጥላለች።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.