የአቪዬሽን ዘርፍ ከብሔራዊ ደኅንነታችን ጋር የተያያዘ ስትራቴጂያዊ ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአቪዬሽን ዘርፍ ከብሔራዊ ደኅንነታችን ጋር የተያያዘ ስትራቴጂያዊ ጉዳይ ነው አሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር)።
በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ለተገኘው ስኬት የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሂዷል።
ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአቪዬሽን ዘርፍ ከሀገራችን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት፣ ከዓለም-አቀፍ ግንኙነትና ከአየር ትራንስፖርት ትስስር ባሻገር ከብሔራዊ ደኅንነታችን ጋር የተያያዘ ስትራቴጂያዊ ጉዳይ ነው።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ስምሪትን ለማጠናከር አደረጃጀቱንና አሠራሩን በማሻሻልና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት በማጠናከር፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ፈጣንና ወቅታዊ ውሳኔ የመስጠት አቅሙን በማሳደግ እንዲሁም ቴክኖሎጂን የተልዕኮ አፈጻጸም ዋና አስቻይ መሣሪያ በማድረግ ባከናወናቸው የሪፎርም ተግባራት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታላቅ ስሙንና የሀገር ኩራት መሆኑን ጠብቆ እንዲቀጥል አግዟል ብለዋል።
የዘርፉ አመራሮችና አባላትም ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጣናዊና ሀገራዊ ፈተናዎችን በመመከት ተልዕኳቸውን በላቀ ደረጃ መወጣታቸውን ገልጸዋል።
ከአቪዬሽን ደኅንነት ጋር በተያያዘ በብሔራዊ ደረጃ የተቀናጀና ቅድመ መከላከልን የሚያስቀድም ሥርዓት እየተጠናከረ እንደሚሄድ፤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ቋሚ ብሔራዊ የአቪዬሽን ስጋት ግምገማና ማስተባበሪያ ሥርዓት እንዲቋቋም እንደሚሠራም አስረድተዋል።
በ2027 ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው ኮፕ-32 ጉባኤ በቂ ዝግጅት እንደሚደረግ እና እየተገነባ የሚገኘው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ታሳቢ ያደረገ አቅምና ሥርዓት እንደሚፈጠር አመልክተዋል።
የአቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አስራት ቀጄላ በበኩላቸው፤ የአቪዬሽን ደኅንነት ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት የሚፈልግ ዘርፍ መሆኑን በማንሳት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ሌሎችንም ኦፕሬተሮችን የሚመጥን አቅም ለመገንባት ርዕይ ተሰንቆ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ ረታ መላኩ አየር መንገዱ በየጊዜው ለሚያሳየው እድገት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአስተማማኝነቱ ተመራጭና እምነት የሚጣልበት ሆኖ እንዲዘልቅ በማድረግ ረገድ ከአየር መንገዱ ርዕይ፣ ስትራቴጂና አሠራር ባሻገር የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ስምሪት ወሳኝ ሚና እንደሚያበረክት አስገንዝበዋል።
በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ የተገኘውን ስኬት በተመለከተ የተለያዩ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በታደሙበት መርሐ-ግብር ላይ በተለያየ ደረጃ የላቀ ሚና ያበረከቱ አባለት እንዲሁም ባለድርሻና ተባባሪ አካላት ዕውቅናና ምስጋና ተበርክቶላቸዋል።