Fana: At a Speed of Life!

አህጉራዊ የአየር ንብረት ድርድር አቅምን ያጠናከረው አረንጓዴ ዐሻራ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት ያከናወነችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በርካታ ውጤት አምጥቷል።

መርሐ ግብሩ ከጀመረበት 2011 ዓ.ም ጀምሮ በበልግ፣ በክረምት እና በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ንቅናቄዎች አማካኝነት ከ56 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

ይህም የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ማስገኘት ጀምሯል። በተለይም በአሁኑ ወቅት የዓለም ከፍተኛ ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው መንገድ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አሳይታለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ወደ ተግባር የገባው የአረንጓዴ ዐሻራ ለዓለም ትምህርት የሚሰጥና በአረአያነት የሚጠቀስ መርሐ ግብር ሆኗል።

መርሐ ግብሩ የአፍሪካን አህጉራዊ የአየር ንብረት ድርድር አቅም የሚገነባ አህጉራዊ ተምሳሌትነቷን ያረጋገጠ ነው።

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ እና በከተማ ልማት ዘርፍ የገነባችው ልምድ አህጉራዊ ኩራት እና ለሌሎች ሀገራት የሚተርፍ ተግባር ሆኗል።

በመርሐ ግብሩ በትኩረት በመሰራቱ የሀገሪቱ የደን ሽፋን አሁን ላይ 23 ነጥብ 6 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ይህንን ምጣኔ ለማሳደግ የመደመር መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።

ህብረተሰቡም በመርሐ ግብሩን ፋይዳ በመገንዘቡ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ጥበቃ የሰጠችው ከፍተኛ ትኩረት የውይይት አጀንዳዎችን ከአዳራሽ ወደ ተግባር በመቀየር ተራቆቱ መሬቶችን በዛፍ መሸፈን ችላለች።

ይህ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ተግባራዊ ውጤት ለሀገራት ተሞክሮ ሆኗል። በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በህዝብ ሰፊ ተሳትፎ መትከል የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቁም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የካርቦን ልቀትን ካሳ የመደራደር አቅምን አጎልብቷል።

አፍሪካውያን አህጉራዊ የመደራደር አቅማቸውን ብቁ በማድረግ ከከፍተኛ የካርቦን ልቀቶች የሚገኘውን ፍትሃዊ ካሳ እንዲያገኙ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ቁልፍ መነሻ ነው። የኢትዮጵያን አህጉራዊ የመሪነት ሚና እና አረንጓዴ ልማት ተሞክሮ በመውሰድ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም አብረው ሊሰሩ ይገባል።

ከነገ ጀምሮ ለ12 ቀናት በቱርክ አንታሊያ ከተማ በሚካሄደው ‘ከቃላት ባለፈ ወደ ተግባርና አፈጻጸም መሸጋገር’ በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የአየር ንብረት ድርድር አቅምን የሚያጠናክሩ ስራዎቿን ይዛ ትቀርባለች።

በአንታሊያ ኤክስፖ ማዕከል ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የሰራቻቸውን በርካታ ተግባራት ለእይታ ታበቃለች።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.