ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ቅድሚያ እና ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው – ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር ጉዳይ ቅድሚያ እና ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ስራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት በ2013 በጀት ዓመት የስራ እድል ፈጠራ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና የክፍለ ከተሞች ስራ አስፈጻሚዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤቱ የ2013 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከማዕከል እስከ ክፍለ ከተማ የተሰሩ ስራዎች አፈጻጸም ሪፖርት የተገመገመ ሲሆን በዘርፉ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ዙሪያ ሰፊ ምክክር ተካሂዷል።
በስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለሴቶች እና ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በማፋጠን ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በከተማዋ ያልተነካ ሰፊ የስራ ዕድል መኖሩን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባዋ ስራን እና ስራ ፈላጊ ዜጎችን በማቀራረብ በኩል ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
በዚህም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ለስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ከእቅድ ጀምሮ እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ቅድሚያ በመስጠት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል።
በተለያዩ ጊዜያት ለስራ ፈጠራ ተብለው የተበተኑ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የብድር ገንዘብ በወቅቱ እንዲመለስ በማድረግ ለቀጣይ ወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ መልሶ ማበደር መቻል አለበትም ነው ያሉት።
ከዚህ በተጨማሪም በመስሪያ ሼዶች አካባቢ የሚስተዋሉ የመብራት አቅርቦት እና የመሰረተ ልማት ችግሮች በአፋጣኝ እንዲፈቱ መናገራቸው ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።