በመዲናዋ የጋራ መንገዶችን ለግል ጥቅም ባዋሉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የጋራ መንገዶችን ለግል ጥቅም በማዋል የተሽከርካሪዎችንና እግረኞችን እንቅስቃሴ እያስተጓጎሉ በሚገኙ አካላት ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በመንገድ ሃብት ላይ የሚፈፀመውን ህገወጥ ድርጊት ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ከመስራት በተጨማሪ ለህገ ወጥ ድርጊቱ ፈጻሚዎች ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ መቆየቱን ገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም ለግል ጥቅም ሲባል የታጠሩና በግንባታ ተረፈ ምርትና ቁሳቁስ የተዘጉ መንገዶችን ከፖሊስና ደንብ ማስከበር አካላት ጋር በጋራ ለተጠቃሚዎች ክፍት የማድረግ ስራ ተጀምሯል ነው የተባለው፡፡
የማስተካከያ እርምጃ ከተወሰደባቸው አካባቢዎች መካከል ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ብስራተ ገብርኤል አካባቢ የሚገኙ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቀጣይም የመንገድ ሃብት ደህንነቱ ተጠብቆ ለታለመለት አገልግሎት ብቻ እንዲውል ለማድረግ መንገድን ለግል ጥቅማቸው በሚያውሉና በመንገድ ልዩ ልዩ ህገ ወጥ ስራዎች በሚሰሩ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።