በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየው የመገጭ ግድብ ግንባታ ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ተባለ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በ5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እየተገነባ ላለው የመገጭ ግድብ ግንባታ መጓተት ምክንያት የሆኑ ችግሮች ተፈተው የግባታ ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ መቀጠሉ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ስራ ተቋራጭነት በ2005 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ግድቡ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከታቀደለት የመጠናቀቂያ ጊዜ ዘግይቷል።
የአማካሪው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ኮርፖሬሽን ተጠሪ መሀንዲስ ይርጋ አበባየ እንደገለጹት፥ ተቋራጩ በቂ ግብዓት ይዞ ወደስራ አለመግባቱ፣ በማሽነሪ እቃዎች ዋጋ መናርና፣ ለአርሶ አደሮች የሚከፈለው ካሳ አፈጻጸም መዘግየት ለግድቡ ግንባታ ሂደት መጓተት ምክንያት ሆኗል።
ችግሩን ለመፍታትም የአካባቢው አስተዳደር እና የፌደራል መንግስት በሰጡት ትኩረት የመፍትሄ እርምጃዎች ተወስደው ግንባታው አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ጃንግዚና ዞንግሚ ለተባሉ ሁለት የቻይና ኩባንያዎች የንዑስ ተቋራጭነት ስራ መሰጠቱም የነበረውን የአቅም ክፍተት መሙላት አስችሏልም ነው ያሉት።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም በበኩላቸው ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዘው ችግር መፈታቱን አስረድተዋል።
በአካባቢው በአሸዋ ማውጣት ስራ የተሰማሩ ወጣቶች ሲያነሱት ለነበረው ቅሬታ መፍትሄ የተሰጠ ሲሆን፥ ግድቡን በቀጣዩ አመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
ለመስኖና ለንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚውለው ይህ ፕሮጀክት በውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለቤትነት በጎንደር ከተማ ጠዳ አካባቢ መገጭ ወንዝ ላይ ነው እየተገነባ ያለው።
የመገጭ ግድብ 185 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ እንደሚይዝ የሚጠበቅ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 116 ሜትር ኪዩብ የሚሆነው በጎንደር ዙሪያና ደንቢያ ወረዳዎች ላሉ አርሶ አደሮች ለመስኖ ልማት የሚውል ነው ተብሏል።
ቀሪው ደግሞ ለጎንደር ከተማና አካባቢው የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲውል የታሰበ ነው።
በነብዩ ዮሐንስ