የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ለፀጥታ ሀይሉ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የባህርዳር ከተማ አስተዳደር በፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ እየወሰዱ ለሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ሃይል አባላት ድጋፍ አደረገ።
በባህርዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ የሚመራ ልዑክ በህግ ማስከበር እርምጃው ለተሰማሩት የፀጥታ ሀይሎች 20 ሰንጋዎችን፣ 6 ሺህ ደርዘን ውሃና መሰል ድጋፎችን ለማዕከላዊ ጎንደር ድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ-ኃይል አስረክበዋል፡፡
ልዑኩ በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የልዩ ኃይል የህክምና ማዕከል በመጎብኘት ሰንጋዎችን ያስረከበ ሲሆን ታካሚዎቹ የገጠማቸውን የብርድ ልብስና የአንሶላ እጥረት ለመፍታት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የፒፒ ከረጢት ፋብርካ ባለቤት አቶ ባይህ መኮንን የተጀመረው ህግን የማስከበር ተግባር በአጭር ጊዜ ተጠናቆ የሁለቱ ህዝቦች ሰላምና ልማት እንዲቀጥል የትግራይ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች ሽብር ፈጣሪ የሆኑ ጥቂት አባላትን ለህግ አሳልፈው መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ልዑኩ ከዚህ በተጨማሪ የጥቃት ሙከራ የተደረገበትን በዳንሻ የሚገኘውን 5ኛ መካናይዝድ ክፍለ ጦር መጎብኘቱን ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።