የፌደራል መንግስት ከህገወጡ የህወሓት ቡድን ጋር ሊደራደር ነው በሚል የተሰራጨው ወሬ ሀሰት ነው- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል መንግስት ከህገወጡ የህወሓት ቡድን ጋር ሊደራደር ነው በሚል የተሰራጨው ወሬ ሀሰት መሆኑ ተገለፀ፡፡
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የፌደራል መንግስትንና ህገወጡን የህወሓት የወንጀለኞች ቡድን የሚያደራድር ልዑክ ሊልኩ ነው በሚል የተሰራጨው ዘገባ ከእውነት የራቀ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር የሆኑትን የሲሪል ራማፎሳን ልዑካን ተቀብለው በግል ይወያያሉ ብሏል።
ሆኖም፣ የፌደራል መንግሥትን እና በህወሓት የሚገኙ ወንጀለኞችን ለማሸማገል ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ በመሰራጨት ላይ የሚገኘው ዜና ሀሰት መሆኑን እናረጋግጣለንም ነው ያለው።
ድርድርን አስመልክቶ የፌደራል መንግሥት ያለው አቋም ፈጽሞ ያልተለወጠም ነው ብሏል መረጃ ማጣሪያው።