Fana: At a Speed of Life!

አቶ ርስቱ ከአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ከአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በክልላዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በዚህ ወቅትም ደቡብ ክልል የበርካታ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መገኛ በመሆኑ ለሀገሪቱ የህብረ ብሄራዊነት ተምሳሌት መሆኑን አቶ ርስቱ ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ የሚስተዋሉ ችግሮች ቢኖሩም ህዝቦች አንድነታቸው እንዲጠናከር በማድረግ በመካከላቸው ጠንካራ የእርስ በርስ ትስስር መፍጠር መቻሉን አውስተዋል።

ብዝሃነትን እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ መልካም እድል በመውሰድ በህዝቦች መካከል የላቀ አንድነት ጎልቶ እንዲወጣ በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት።

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን እንደ ሀገር በጋራ ለመቆም የሚያደርገውን ሁሉን አቀፍ ጥረት የክልሉ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሰብሳቢ ዶክተር ጣሰው ገብሬ በበኩላቸው፥ ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ውስጣዊ አደረጃጀቱን በማጠናከር ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውሰዋል።

ክልሉ የህብረ ብሄራዊነት ተምሳሌት ሆኖ መቆየቱ በሀገሪቱ በአብነት የሚጠቀስ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፥ ኮሚሽኑ የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮችን ብቻ በማየት የህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ጠንካራ ሀገር ለመመስረት እና ህብረ ብሄራዊነት እንዲጎለብት ክልሉ እያከናወነ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑም የኮሚሽኑ አባላት ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.